Ezekiel 38

በጎግ ላይ የተነገረ ትንቢት

1  የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 2“የሰው ልጅ ሆይ፤ ፊትህን በማጎግ ምድር በሚገኘው፣ በሞሳሕና በቶቤል ዋና አለቃ
ወይም የሮሽ አለቃ
በጎግ ላይ አድርግ፤ በእርሱ ላይ ትንቢት ተናገር፤
3እንዲህም በል፤ ጌታ  እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የሞሳሕና የቶቤል ዋና አለቃ
ወይም የሮሽ አለቃ ጎግ
ጎግ ሆይ፤ ተነሥቼብሃለሁ።
4ወደ ኋላ እመልስሃለሁ፤ መንጋጋህ ውስጥ መንጠቆ አስገብቼ ከመላው ሰራዊትህ ጋር፣ ፈረሶችህን፣ ፈረሰኞችህን ከነሙሉ ትጥቃቸው፣ ትልቅና ትንሽ ሰይፍ የያዙትን ሁሉ፣ ሰይፋቸውንም የወለወሉትን ሁሉ አስወጣለሁ። 5ጋሻ የያዙና የራስ ቍር የደፉት ሁሉ፣ ፋርስ፣ ኢትዮጵያና ፉጥ ከእነርሱ ጋር ይሆናሉ። 6ደግሞም ጎሜርን ከወታደሮቹ ጋር፣ ራቅ ካለው ሰሜንም የቴርጋማን ቤት ከወታደሮቹ ሁሉ ጋር ብዙ ሕዝቦችን ከአንተ ጋር አስወጣለሁ።”

7“ ‘አንተና በዙሪያህ የተሰበሰቡት ሁሉ ተነሡ፤ ተዘጋጁ፤ አንተም መሪያቸው ሁን። 8ከብዙ ቀን በኋላ ለጦርነት ትጠራለህ። በኋለኛው ዘመንም ከጦርነት ያገገመችውን፣

ሕዝቧ ከአያሌ አሕዛብ መካከል ወጥቶ የተሰበሰበውን፣ ለብዙ ጊዜ ባድማ በነበረው በእስራኤል ተራሮች ላይ የሰፈረውን ወገን ትወራለህ። ከሕዝቦች መካከል ወጥተው፣ አሁን ሁሉም በሰላም ይኖራሉ።
9አንተና ወታደሮችህ ሁሉ፣ ከአንተም ጋር ያሉት ብዙ ሕዝቦች እንደ ማዕበል ትወጣላችሁ፤ ምድርን እንደሚሸፍን ደመናም ትሆናላችሁ።

10“ ‘ጌታ  እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በዚያ ቀን ሐሳብ ወደ አእምሮህ ይመጣል፤ ክፋትንም ታውጠነጥናለህ።” 11እንዲህም ትላለህ፤ “ቅጥር የሌላቸውን መንደሮች ምድር እወራለሁ፤ ሁሉም ያለ ቅጥር፣ ያለ በርና ያለ ብረት መወርወሪያ የሚኖረውን፣ ሰላማዊና ያለ ሥጋት የተቀመጠውን ሕዝብ እወጋለሁ፤ 12እዘርፋለሁ፤ እነጥቃለሁ፤ እንዲሁም ከአሕዛብ ተሰባስቦ እንደ ገና በሰፈረው፣ በከብትና በሸቀጥ በከበረው፣ በምድሪቱም መካከል በሚኖረው ሕዝብ ላይ እጄን አነሣለሁ።” 13ሳባና ድዳን፣ የተርሴስ ነጋዴዎችና መንደሮቿም ሁሉ
ወይም ጠንካራ መንደሮችዋ
እንዲህ ይሉሃል፤ “ልትዘርፍ መጣህን? ሰራዊትህን ያሰባሰብኸው ለመበዝበዝ፣ ወርቅና ብሩን አጋብሶ ለመሄድ፣ ከብቱንና ሸቀጡን ለመውሰድ፣ ብዙ ምርኮ ይዞ ለመመለስ ነውን?” ’

14“ስለዚህ የሰው ልጅ ሆይ፤ ትንቢት ተናገር፤ ጎግንም እንዲህ በለው፤ ‘ጌታ  እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በዚያ ቀን ሕዝቤ እስራኤል በሰላም መቀመጡን ዐውቀህ አትንቀሳቀስምን? 15በስተ ሰሜን ርቆ ከሚገኘው ቦታ ትመጣለህ፤ አንተና ከአንተም ጋር ብዙ ሕዝቦች፣ እጅግ ታላቅ ኀያል ሰራዊትም በፈረሶች ላይ ሆናችሁ ትመጣላችሁ። 16ምድርን እንደሚሸፍን ደመና ሆነህ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ትወጣለህ። ጎግ ሆይ፤ በፊታቸው ቅድስናዬን ስገልጥ ሕዝቦች እኔን ያውቁ ዘንድ በኋለኛው ዘመን በምድሬ ላይ አመጣሃለሁ።”

17“ ‘ጌታ  እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በቀደመው ዘመን በባሪያዎቼ በእስራኤል ነቢያት ስለ እርሱ የተናገርሁለት ያ ሰው አንተ አይደለህምን? በዚያን ወቅት አንተን በእነርሱ ላይ እንደማመጣባቸው ለብዙ ዓመታት ትንቢት ተናገሩ።” 18በዚያን ጊዜ እንዲህ ይሆናል፤ “ጎግ የእስራኤልን ምድር ሲወጋ፣ ብርቱ ቍጣዬ ይነሣሣል፤ ይላል ጌታ  እግዚአብሔር 19በዚያን ጊዜ በቅናቴና በሚያስፈራው ቍጣዬ በእስራኤል ታላቅ የምድር መንቀጥቀጥ ይሆናል ብዬ ተናግሬአለሁ። 20የባሕር ዓሦች፣ የሰማይ ወፎች፣ የምድር አራዊት፣ በምድር ላይ የሚሳብ ማንኛውም ፍጡር፣ እንዲሁም በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ፣ በፊቴ ይንቀጠቀጣሉ፤ ተራሮች ይገለባበጣሉ፤ ገደሎች ይናዳሉ፤ 21በተራሮቼም ሁሉ በጎግ ላይ ሰይፍ እጠራለሁ፤ ይላል ጌታ  እግዚአብሔር፤ የእያንዳንዱም ሰው ሰይፍ በወንድሙ ላይ ያርፋል። 22በቸነፈርና በደም መፋሰስ እፈርድበታለሁ፤ የዝናብ ዶፍ፣ የበረዶ ድንጋይ፣ የሚያቃጥል ድኝ፣ በእርሱና በወታደሮቹ፣ ከእርሱም ጋር ባሉት ሕዝቦች ላይ አወርዳለሁ። 23በዚህም ታላቅነቴንና ቅድስናዬን አሳያለሁ፤ በብዙ ሕዝቦች ፊት ራሴን አሳውቃለሁ፤ ከዚያም እኔ  እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ።” ’
Copyright information for AmhNASV