Jeremiah 30

የእስራኤል ሕዝብ መመለስ

1  ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው፤ 2“የእስራኤል አምላክ  እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የነገርሁህን ቃል ሁሉ በመጽሐፍ ጻፈው። 3እነሆ፣ ሕዝቤን እስራኤልንና ይሁዳን’ ይላል  እግዚአብሔር፤ ‘ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠኋት ምድር የምመልስበት ጊዜ ተቃርቦአል፤
ወይም የሕዝቤን የእስራኤልንና የይሁዳን ዕድል ፈንታ እመልሳለሁ
እነርሱም ይወርሷታል’ ይላል  እግዚአብሔር።”

4 እግዚአብሔር ስለ እስራኤልና ስለ ይሁዳ የተናገረው ቃል ይህ ነው፤ 5 “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ ‘የፍርሀትና የሽብር ጩኸት ተሰምቶአል፤
ሰላምም የለም።

6 እስቲ ጠይቁ፤ ተመልከቱም፤
ወንድ መውለድ ይችላል?
ታዲያ ወንድ ሁሉ ምጥ እንደ ያዛት ሴት፣
እጁን በሆዱ ላይ አድርጎ፣
የሰውስ ሁሉ ፊት ጠቍሮ የማየው ለምንድን ነው?

7 ያ ቀን ምንኛ አስጨናቂ ይሆናል!
እንደዚያም ያለ አይኖርም፤
ለያዕቆብ የመከራ ጊዜ ነው፤
ነገር ግን ይተርፋል።


8 “ ‘በዚያን ቀን’ ይላል የሰራዊት ጌታ  እግዚአብሔር
‘በጫንቃቸው ላይ ያለውን ቀንበር እሰብራለሁ፤
እስራታቸውንም እበጥሳለሁ፤
ከእንግዲህ ባዕዳን አይገዙአቸውም።

9 ነገር ግን ለአምላካቸው  ለእግዚአብሔር
ለማስነሣላቸውም ለንጉሣቸው፣
ለዳዊት ይገዛሉ።

10 “ ‘ስለዚህ፤ አገልጋዬ ያዕቆብ ሆይ፤ አትፍራ፤
እስራኤል ሆይ፤ አትደንግጥ፤’
ይላል  እግዚአብሔር
‘አንተን ከሩቅ አገር፣
ዘርህንም ከተማረኩበት ምድር እታደጋለሁ፤
ያዕቆብ ተመልሶ በሰላምና በርጋታ ይቀመጣል፣
የሚያስፈራውም አይኖርም።

11 እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፤ አድንሃለሁም፣
ይላል  እግዚአብሔር
‘በአሕዛብ መካከል በትኜሃለሁ፤
እነዚህን አሕዛብ ሁሉ ፈጽሜ አጠፋለሁ፤
አንተን ግን ሙሉ በሙሉ አላጠፋህም፤
በመጠኑ እቀጣሃለሁ እንጂ፣
ያለ ቅጣት አልተውህም።

12 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ ‘ስብራትህ የማይጠገን፣
ቍስልህም የማይድን ነው።

13 የሚሟገትልህ ሰው የለም፤
ለቍስልህ መድኃኒት አይኖርም፤
ፈውስም አታገኝም።

14 ወዳጆችህ ሁሉ ረስተውሃል፤
ስለ አንተም ግድ የላቸውም።
ጠላት እንደሚመታ መታሁህ፤
እንደ ጨካኝም ቀጣሁህ፤
በደልህ ታላቅ፣
ኀጢአትህም ብዙ ነውና።

15 ፈውስ ለማይገኝለት ሕመምህ፣
ስለቍስልህ ለምን ትጮኻለህ?
በደልህ ታላቅ፣ ኀጢአትህም ብዙ ስለ ሆነ፣
እነዚህን ሁሉ አድርጌብሃለሁና።


16 “ ‘ነገር ግን አሟጠው የበሉህ ሁሉ እንደዚያው ይበላሉ፤
ጠላቶችህ ሁሉ ለምርኮ ዐልፈው ይሰጣሉ፤
የሚዘርፉህ ይዘረፋሉ፤
የሚበዘብዙህም ሁሉ ይበዘበዛሉ።

17 አንተን ግን መልሼ ጤነኛ አደርግሃለሁ፤
ቍስልህንም እፈውሳለሁ፤’
ይላል  እግዚአብሔር
“ ‘የተናቀች፣
ማንም የማይፈልጋት ጽዮን” ብለውሃልና።’

18 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ ‘እነሆ የያዕቆብን ድንኳን ምርኮ እመልሳለሁ፤
ለማደሪያውም እራራለሁ፤
ከተማዪቱ በፍርስራሿ ጒብታ ላይ ትሠራለች፤
ቤተ መንግሥቱም በቀድሞ ቦታው ይቆማል።

19 ከእነርሱም የምስጋና መዝሙር፣
የእልልታ ድምፅ ይሰማል።
እኔ አበዛቸዋለሁ፤
ቍጥራቸውም አይቀንስም፣
አከብራቸዋለሁ፤
የተናቁም አይሆኑም።

20 ልጆቻቸው እንደ ቀድሞው ይሆናሉ፤
ማኅበረ ሰቡም በፊቴ የጸና ይሆናል፤
የሚጨቍኗቸውን ሁሉ እቀጣለሁ።

21 መሪያቸው ከራሳቸው ወገን ይሆናል፤
ገዣቸውም ከመካከላቸው ይነሣል፤
ወደ እኔ አቀርበዋለሁ፤ እርሱም ይቀርበኛል፤
አለዚያማ ደፍሮ፣
ወደ እኔ የሚቀርብ ማን ነው?
ይላል  እግዚአብሔር

22 “ ‘ስለዚህ እናንተ ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ፤
እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ።’ ”


23 እነሆ፣  የእግዚአብሔር ማዕበል፣
በቍጣ ይነሣል፤
የሚገለባብጥም ዐውሎ ነፋስ፣
በክፉዎች ዐናት ላይ ይወርዳል።

24 የልቡን ሐሳብ ሳይፈጽም፣
 የእግዚአብሔር ቍጣ፣
እንዲሁ አይመለስም፤
በሚመጡትም ዘመናት፣
ይህን ታስተውላላችሁ።
Copyright information for AmhNASV