Jeremiah 47
ስለ ፍልስጥኤማውያን የተነገረ መልእክት
1ፈርዖን ጋዛን ድል ከማድረጉ በፊት፣ ስለ ፍልስጥኤማውያን ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው፤ 2 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ በሰሜን በኩል ውሃ እየሞላ ነው፣ኀይለኛ ጐርፍ ይሆናል፤
አገሪቷንና በውስጧ ያሉትንም ሁሉ፣
ከተሞቿንና ነዋሪዎቻቸውን ያጥለቀልቃል።
ሕዝቡም ድምፁን ከፍ አድርጎ ይጮኻል፤
የምድሪቱ ነዋሪ ሁሉ ዋይ ዋይ ይላል፤
3 ከፈረስ ኮቴ ድምፅ፣
ከጠላት ሠረገላ ጩኸትና፣
ከሠረገላው ሽክርክሪት ፍትጊያ ድምፅ የተነሣ፣
አባቶች ልጆቻቸውን ለመርዳት ወደ ኋላ መለስ አይሉም፤
እጃቸውም ስንኩል ይሆናል።
4 ፍልስጥኤማውያንን ሁሉ ለማጥፋት፣
ተርፈውም የሚረዷቸውን ሁሉ፣
ከጢሮስና ከሲዶና ለመቍረጥ፣
ቀኑ ደርሶአልና።
እግዚአብሔር በከፍቶር ▼
▼ ቀርጤስ ነው
ዳርቻ የቀሩትን፣ ፍልስጥኤማውያንን ሊያጠፋተነሥቶአል።
5 ጋዛ በማዘን ራሷን ትላጫለች፣
አስቀሎና አፏን ትይዛለች።
በሜዳማ ስፍራ የምትገኙ ትሩፋን ሆይ፤
እስከ መቼ ሰውነታችሁን ትቧጥጣላችሁ?
6 “ ‘ የእግዚአብሔር ሰይፍ ሆይ፤
የማታርፈው እስከ መቼ ነው?
ወደ ሰገባህ ተመልሰህ ግባ፤
ጸጥ ብለህ ተቀመጥ’ ትላላችሁ።
7 ነገር ግን እግዚአብሔር አስቀሎናንና የባሕሩን ዳርቻ፣
እንዲወጋ ሲያዝዘው፣
እንዲፈጽመውም ትእዛዝ ሲሰጠው፣
እንዴት ማረፍ ይችላል?”
Copyright information for
AmhNASV