Judges 20

እስራኤላውያን ከብንያማውያንጋር ተዋጉ

1ከዚያም ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ያሉ እንዲሁም በገለዓድ ምድር የሚገኙ እስራኤላውያን ሁሉ እንደ አንድ ሰው ሆነው ወጡ፤ በምጽጳም  በእግዚአብሔር ፊት ተሰበሰቡ። 2የእስራኤል ሕዝብ ነገዶች ሁሉ ቍጥራቸው አራት መቶ ሺህ በሚሆን፣ ሰይፍ በሚመዙ እግረኞች ወታደሮች በሆኑ በእግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ መካከል ተገኙ። 3በዚህ ጊዜ ብንያማውያን፣ እስራኤላውያን ወደ ምጽጳ መውጣታቸውን ሰሙ፤ ከዚያም እስራኤላውያን፣ “ይህ ክፉ ድርጊት እንዴት እንደ ተፈጸመ እስቲ ንገሩን” ተባባሉ።

4ስለዚህ የተገደለችው ሴት ባል ሌዋዊ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እኔና ቍባቴ በዚያ ለማደር በብንያም ወደምትገኘው ወደ ጊብዓ መጣን። 5የጊብዓም ሰዎች በሌሊት ሊገድሉኝ ያደርኩበትን ቤት ከበቡት፤ ከዚያም በቁባቴ ላይ ስለ አመነዘሩባት ሞተች። 6የቁባቴንም ሬሳ ከቈራረጥሁ በኋላ እያንዳንዱን ቍራጭ፣ እያንዳንዱ የእስራኤል ርስት ወዳለበት አገር ሰደድሁ፤ ይህን ያደረግሁትም ሰዎቹ በእስራኤል ዘንድ አሠቃቂና አስነዋሪ ድርጊት ስለ ፈጸሙ ነው። 7አሁንም እናንተ እስራኤላውያን ሁሉ በጒዳዩ ላይ ተወያዩበት፤ ፍርዳችሁንም ስጡ።”

8ከዚያም ሕዝቡ እንደ አንድ ሰው ሆነው በመነሣት እንዲህ አሉ፤ “ከእኛ ማንም ሰው ወደ ድንኳኑ አይሄድም፤ ማንኛችንም ወደ ቤታችን አንመለስም። 9ነገር ግን በጊብዓ ላይ የምናደርገው ይህ ነው፤ በዕጣው መሠረት እንዘምትበታለን። 10ከመላው የእስራኤል ነገዶችም ለሰራዊቱ ስንቅ እንዲይዙ፣ ከመቶው ዐሥር፣ ከሺው አንድ መቶ፣ ከዐሥር ሺው ደግሞ አንድ ሺህ ሰው እንወስዳለን። ከዚያም ሰራዊቱ በብንያም ወደምትገኘው ጊብዓ በሚደርስበት ጊዜ፣ ነዋሪዎችዋ በእስራኤል ላይ ለፈጸሙት አስነዋሪ ድርጊት ተገቢውን ቅጣት ይሰጣቸዋል።” 11ስለዚህ የእስራኤል ሰዎች ሁሉ እንደ አንድ ሰው ሆነው በመተባበር በከተማዪቱ ላይ ዘመቱባት።

12የእስራኤል ነገዶች ለመላው የብንያም ነገድ እንዲህ በማለት መልእክተኞች ላኩ፣ “በመካከላችሁ የተፈጸመው ይህ ክፉ ድርጊት ምንድ ነው? 13አሁንም እነርሱን ገድለን ይህን ክፉ ድርጊት ከእስራኤል እንድናስወግድ፣ እነዚያን የጊብዓን ወስላቶች አሳልፋችሁ ስጡን።”

ብንያማውያን ግን ወገኖቻቸውን እስራኤላውያንን አልሰሟቸውም ነበር፤
14ስለዚህ እስራኤላውያንን ለመውጋት ከየከተሞቻቸው በአንድነት ወደ ጊብዓ መጡ። 15ብንያማውያንም ከመላው የጊብዓ ነዋሪዎች መካከል ከተመረጡት ሰባት መቶ ሰዎች ሌላ፣ ሰይፍ የታጠቁ ሃያ ስድስት ሺህ ሰዎች በአንድ አፍታ ከየከተሞቻቸው በተጨማሪ አሰባሰቡ። 16በእነዚህም ሁሉ መካከል እያንዳንዳቸው ድንጋይ ወንጭፈው ጠጒር እንኳ የማይስቱ ሰባት መቶ ምርጥ ግራኞች ነበሩ።

17እስራኤላውያን፣ ብንያማውያንን ሳይጨምር፣ ሰይፍ የታጠቁ አራት መቶ ሺህ ተዋጊዊች አሰባሰቡ።

18እስራኤላውያን ወደ ቤቴል
ወይም ወደ እግዚአብሔር ቤት፤ በቁ 26 ላይም እንደዚሁ
ወጡ፤ እግዚአብሔርንም፣ “ብንያማውያንን ለመውጋት ከመካከላችን ማን ቀድሞ ይውጣ?” ሲሉ ጠየቁ።

 እግዚአብሔርም፣ “ይሁዳ ቀድሞ ይውጣ” ብሎ መለሰ።

19በማግሥቱ ጧት እስራኤላውያን ተነሥተው በጊብዓ አጠገብ ሰፈሩ፤ 20የእስራኤል ሰዎች ብንያማውያንን ለመውጋት ሄዱ፤ በጊብዓ ለሚያደርጉትም ውጊያ ቦታ ቦታቸውን ያዙ። 21ብንያማውያን ከጊብዓ ወጡ፤ በዚያችም ዕለት ከእስራኤላውያን ሃያ ሁለት ሺህ ሰዎች ገደሉ። 22ይሁን እንጂ እስራኤላውያን እርስ በርሳቸው ተበረታትተው በመጀመሪያው ቀን ተሰልፈው በነበረበት ስፍራ ላይ እንደ ገና ቦታ ቦታቸውን ያዙ። 23እስራኤላውያን ወጥተው እስኪመሽ ድረስ  በእግዚአብሔር ፊት አለቀሱ፤ “ወንድሞቻችንን ብንያማውያንን ለመግጠም እንደ ገና እንውጣን?” ብለው  እግዚአብሔርን ጠየቁ።

 እግዚአብሔርም፣ “አዎን፤ ውጡና ግጠሟቸው” ብሎ መለሰላቸው።

24በሁለተኛው ቀን እስራኤላውያን ወደ ብንያማውያን ተጠጉ። 25በዚሁ ጊዜም ብንያማውያን፣ እስራኤላውያንን ሊወጉ ከጊብዓ ወጡ፤ እንደ ገናም በሙሉ ሰይፍ የታጠቁ ዐሥራ ስምንት ሺህ ሰዎች ገደሉ።

26የእስራኤልም ሕዝብ ሁሉ ወደ ቤቴል ወጡ፤ እዚያም እያለቀሱ  በእግዚአብሔር ፊት ተቀመጡ፤ በዚያን ቀን እስኪመሽ ድረስ ጾሙ፤  በእግዚአብሔር ፊት የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት
በትውፊት የሰላም መስዋዕት ይባላል።
አቀረቡ።
27እስራኤላውያንም  የእግዚአብሔርን ፈቃድ ጠየቁ፤ በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔር የኪዳኑ ታቦት እዚያው ነበር፤ 28የአሮን ልጅ፤ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስም በፊቱ ይቆም ነበር። እስራኤላውያንም፣ “ወንድሞቻችንን ብንያማውያንን እንደ ገና ሄደን ጦርነት እንግጠማቸው ወይስ ይቅር?” ሲሉ ጠየቁ።

 እግዚአብሔርም፣ “ሂዱ፤ በነገው ዕለት በእጃችሁ እሳልፌ እሰጣችኋለሁ” አላቸው።

29ከዚያም እስራኤላውያን በጊብዓ ዙሪያ ድብቅ ጦር አኖሩ። 30በሦስተኛውም ቀን ብንያማውያንን ለመውጋት ወጡ፤ ከዚህ በፊት እንዳደረጉት ሁሉ ጊብዓን ለመውጋት ቦታ ቦታቸውን ያዙ። 31ብንያማውያንም ሊገጥሟቸው ወጡ፤ ከከተማዪቱም ርቀው እንዲሄዱ ተደረጉ፤ እንደ በፊቱም እስራኤላውያንን ይገድሉ ጀመር። ከዚህ የተነሣም በሜዳው እንዲሁም ወደ ቤቴልና ወደ ጊብዓ በሚወስደው መንገዶች ላይ ሠላሳ ያህል ሰዎች ወድቀው ነበር።

32ብንያማውያኑ፣ “እንደ በፊቱ ይኽው ድል እያደረግናቸው ነው” አሉ፣ እስራኤላውያንም በበኩላቸው፣ “ወደ ኋላ እያፈገፈግን ከከተማዪቱ ወደ መንገዶቹ እንዲርቁ እናድርጋቸው” ይሉ ነበር።

33የእስራኤል ሰዎች በሙሉ ከነበሩበት ቦታ አፈግፍገው በበኣልታማር ስፍራ ስፍራቸውን ያዙ። ሸምቆ ይጠባበቅ የነበረው የእስራኤል ጦር ደግሞ ካደፈጠበት ከጊብዓ በስተ ምዕራብ
አንዳንድ የሰብዓ ሊቃናት ትርጒሞች ቩልጌት ከዚህ ጋር ይስማማሉ ነገር ግን የዕብራይስጡ ቃል ትርጒም በትክክል አይታወቅም።
ካለው ቦታ ወጣ።
34ከዚያም ከመላው እስራኤል የተውጣጣው ዐሥር ሺህ ጦር በጊብዓ ላይ ፊት ለፊት አደጋ ጣለ። ውጊያው ከመበርታቱ የተነሣም፣ ብንያማውያን መጥፊያቸው እየቀረበ መምጣቱን ገና አላወቁም ነበር። 35እግዚአብሔር ብንያምን በእስራኤል ፊት መታው፤ በዚያችም ዕለት እስራኤላውያን በሙሉ ሰይፍ የታጠቁ ሃያ አምስት ሺህ አንድ መቶ ብንያማውያንን ገደሉ። 36ከዚህ የተነሣ ብንያማውያን ድል መሆናቸውን ተረዱ።

በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን ጊብዓ ላይ ባኖሩት ድብቅ ጦር ስለ ተማመኑ የተሸነፉ በመምሰል ለብንያማውያን ቦታ ለቀቁ።
37ከዚያም ሸምቀው የነበሩት ሰዎች በድንገት እየተወረወሩ ወደ ጊብዓ ገቡ፤ በየቦታው ተሰራጭተውም መላዪቱን ከተማ በሰይፍ መቱ። 38የእስራኤል ሰዎች ያሸመቀው ጦር በከተማዪቱ ውስጥ ከባድ የጢስ ደመና ምልክት እንዲያሳይ፤ 39እስራኤላውያንም ይህን ሲያዩ ወዲያውኑ እንዲያፈገፍጉ ተስማሙ።

ብንያማውያንን ማጥቃት እንደ ጀመሩ፣ ሠላሳ እስራኤላውያንን ስለ ገደሉ፣ “እንደ መጀመሪያው የጦርነት ጊዜ እያሸነፍናቸው ነው” አሉ።
40ነገር ግን የጢሱ ዐምድ ከከተማዪቱ መነሣት በጀመረ ጊዜ፣ ብንያማውያን ወደ ኋላቸው ዞረው የመላዪቱ ከተማ ጢስ ወደ ሰማይ ሲወጣ አዩ። 41ከዚያም እስራኤላውያን ዞረው አጠቋቸው፤ በዚህ ጊዜ ብንያማውያን ጥፋት እንደ ደረሰባቸው ስላወቁ እጅግ ደነገጡ። 42ስለዚህም ጀርባቸውን አዙረው ከእስራኤላውያን ፊት ወደ ምድረ በዳው ሸሹ፤ ሆኖም ከጦርነት ማምለጥ አልቻሉም፤ ከየከተሞቹ የወጡ እስራኤላውያንም በዚያው ገደሏቸው። 43ብንያማውያንንም ከበቧቸው፤ አሳደዷቸው፤ ከጊብዓ በስተ ምሥራቅ ትይዩ ባለውም ስፍራ በቀላሉ
የዕብራይስጡ ቃል ትርጒም በትክክል አይታወቅም።
አሸነፏቸው፤
44በጦርነቱም ላይ ዐሥራ ስምንት ሺህ ብንያማውያን ወደቁ፤ ሁሉም ምርጥ ተዋጊዎች ነበሩ። 45ብንያማውያን ጀርባቸውን አዙረው በምድረ በዳው በኩል ወደ ሬሞን ዐለት በሚሸሹበት ጊዜ፣ እስራኤላውያን በመንገድ ላይ አምስት ሺህ ሰው ገደሉባቸው፤ እስከ ጊድአምም ድረስ ተከታትለው ሁለት ሺህ ሰዎች በተጨማሪ ገደሉ።

46በዚያች ዕለት ሰይፍ የታጠቊ ሃያ አምስት ሺህ ብንያማውያን በጦር ሜዳ ወደቊ፤ ሁሉም ምርጥ ተዋጊዎች ነበሩ። 47ነገር ግን ስድስት መቶ ሰዎች ጀርባቸውን አዙረው በምድረ በዳው ውስጥ ወዳለው ወደ ሬሞን ዐለት ሸሹ፤ በዚያም አራት ወር ተቀመጡ። 48ከዚያም እስራኤላውያን ወደ ብንያም ምድር ተመልሰው ከተሞቻቸውን በሙሉ እንዲሁም እንስሳቱንና በዚያ ያገኙትን ሁሉ በሰይፍ መቱ፤ በመንገዳቸው ያገኙትን ከተማ ሁሉ በእሳት አቃጠሉ።
Copyright information for AmhNASV