Lamentations 4


1
ይህ ምዕራፍ፣ ጥቅሶቹ ተከታታይ ፊደላት ባሉት የዕብራይስጥ ሆህያት የሚጀምር ቃል ወይም ዐረፍተ ነገር ያለው ግጥም ነው።
ወርቁ እንዴት ደበሰ!
ንጹሑስ ወርቅ እንዴት ተለወጠ!
የከበሩ ድንጋዮች፣
በየመንገዱ ዳር ተበታትነዋል።


2 እንደ ወርቅ ይቈጠሩ የነበሩ፣
የከበሩ የጽዮን ወንዶች ልጆች፣
የሸክላ ሠሪ እጅ እንደ ሠራው፣
እንዴት አሁን እንደ ሸክላ ዕቃ ሆኑ!


3 ቀበሮዎች እንኳን ግልገሎቻቸውን ለማጥባት፣
ጡታቸውን ይሰጣሉ፤
ሕዝቤ ግን በምድረ በዳ እንዳሉ ሰጎኖች፣
ጨካኞች ሆኑ።


4 ከውሃ ጥም የተነሣ፣
የሕፃናት ምላስ ከላንቃቸው ጋር ተጣበቀ፤
ልጆቹ ምግብ ለመኑ፤
ነገር ግን ማንም አልሰጣቸውም።


5 ምርጥ ምግብ ይበሉ የነበሩ፣
ተቸግረው በየመንገዱ ላይ ተንከራተቱ፤
ሐምራዊ ግምጃ ለብሰው ያደጉ፣
አሁን በዐመድ ክምር ላይ ተኙ።


6 በሕዝቤ ላይ የደረሰው ቅጣት፣
የማንም እጅ ሳይረዳት፣
በድንገት ከተገለበጠችው፣
ሰዶም ላይ ከደረሰው ቅጣት ይልቅ ታላቅ ነው።

7 መሳፍንቶቻቸው ከበረዶ ይልቅ ብሩህ፣
ከወተትም ይልቅ ነጭ ነበሩ፤
ሰውነታቸው ከቀይ ዕንቍ የቀላ፣
መልካቸውም እንደ ሰንፔር
ወይም ላፒስ ላዙሊ
ነበር።


8 አሁን ግን ከጥላሸት ይልቅ ጠቍረዋል፤
በመንገድም የሚያውቃቸው የለም፤
ቆዳቸው ከዐጥንታቸው ጋር ተጣብቆአል፤
እንደ ዕንጨትም ደርቀዋል።


9 በራብ ከሚሞቱት ይልቅ፣
በሰይፍ የተገደሉት ይሻላሉ፤
ምግብ በሜዳ ላይ ካለማግኘታቸው የተነሣ፣
በራብ ደርቀው ያልቃሉ።


10 ሕዝቤ ባለቀበት ጊዜ፣
ምግብ እንዲሆኑአቸው፣
ርኅሩኆቹ ሴቶች በገዛ እጆቻቸው፣
ልጆቻቸውን ቀቀሉ።


11  እግዚአብሔር ለመቅሠፍቱ መውጫ በር ከፈተ፤
ጽኑ ቍጣውን አፈሰሰ፤
መሠረትዋን እንዲበላ፣
በጽዮን እሳት ለኰሰ።


12 ጠላቶችም ሆኑ ወራሪዎች፣
የኢየሩሳሌምን በሮች ጥሰው ይገባሉ ብለው፣
የምድር ነገሥታት፣
ወይም ከዓለም ሕዝብ አንዳቸውም አላመኑም።


13 ይህ ግን ከነቢያት ኀጢአት፣
ከካህናቷም መተላለፍ የተነሣ ሆኖአል፤
በውስጧ፣
የጻድቃንን ደም አፍስሰዋልና።


14 እንደ ታወሩ ሰዎች፣
በየመንገዱ ላይ ይደናበራሉ፤
ማንም ሰው ደፍሮ ልብሳቸውን መንካት እስከማይችል ድረስ፣
በደም እጅግ ረክሰዋል።


15 ሰዎች “ሂዱ! እናንት ርኵሳን!” ብለው ይጮኹባቸዋል፤
“ወግዱ! ወግዱ! አትንኩ!” ይሏቸዋል፤
ሸሽተው በሚቅበዘበዙበትም ጊዜ፣
በአሕዛብ መካከል ያሉ ሰዎች፣
“ከእንግዲህ በዚህ መቀመጥ አይገባቸውም!” ይላሉ።

16  እግዚአብሔር ራሱ በትኖአቸዋል፤
ከእንግዲህ ወዲያ አይጠብቃቸውም፤
ካህናቱ አልተከበሩም፤
ሽማግሌዎቹም ከበሬታ አላገኙም።


17 ከሁሉም በላይ በከንቱ ርዳታን ስንጠባበቅ፣
ዐይኖቻችን ደከሙ፤
ከግንብ ማማችን ላይ ሆነን፣
ሊያድን ከማይችል ሕዝብ ርዳታ ጠበቅን።


18 ሰዎች እግር እግራችንን ተከታተሉን፤
ስለዚህ በመንገዳችን መሄድ አልቻልንም፤
መጨረሻችን ቀርቦአል፤ ቀኖቻችንም ተቈጥረዋል፤
ፍጻሜያችን መጥቶአልና።


19 ከሰማይ ንስሮች ይልቅ፣
ጠላቶቻችን ፈጣኖች ናቸው፤
በተራሮች ላይ አሳደዱን፤
በምድረ በዳም ሸመቁብን።


20 በእግዚአብሔር የተቀባው፣ የሕይወታችን እስትንፋስ፣
በወጥመዳቸው ተያዘ፤
በጥላው ሥር፣
በአሕዛብ መካከል እንኖራለን ብለን አስበን ነበር።


21 አንቺ በዖፅ ምድር የምትኖሪ፣
የኤዶምያስ ሴት ልጅ ሆይ፤ ደስ ይበልሽ፤ ሐሴትም አድርጊ
ነገር ግን ለአንቺም ደግሞ ጽዋው ይደርስሻል፤
ትሰክሪያለሽ፤ ዕርቃንሽንም ትጋለጫለሽ።


22 የጽዮን ልጅ ሆይ፤ ቅጣትሽ ያበቃል፤
እርሱም የስደትሽን ዘመን አያራ ዝምም፤
ነገር ግን አንቺ የኤዶምያስ ልጅ ሆይ፤
ኀጢአትሽን ይቀጣል፤
ክፋትሽንም ይፋ ያወጣል።

Copyright information for AmhNASV