Psalms 38

የጭንቅ ሰዓት ጸሎት

የዳዊት መዝሙር፤ ለመታሰቢያ


1  እግዚአብሔር ሆይ፤ በቍጣህ አትገሥጸኝ፤
በመዓትህም አትቅጣኝ።

2 ፍላጻዎችህ ወግተውኛልና፤
እጅህም ተጭናኛለች።

3 ከቍጣህ የተነሣ ሰውነቴ ጤና አጥቶአል፤
ከኀጢአቴም የተነሣ ዐጥንቶቼ ሰላም የላቸውም።

4 በደሌ ውጦኛል፤
እንደ ከባድ ሸክምም ተጭኖኛል።


5 ከንዝህላልነቴ የተነሣ፣
ቍስሌ ሸተተ፤ መገለም፤

6 ዐንገቴን ደፋሁ፤ ጐበጥሁም፤
ቀኑንም ሙሉ በትካዜ ተመላለስሁ።

7 ወገቤ እንደ እሳት ነዶአል፤
ሰውነቴም ጤና የለውም።

8 እጅግ ዝያለሁ፤ ፈጽሞም ደቅቄአለሁ፤
ከልቤም መታወክ የተነሣ እጮኻለሁ።


9 ጌታ ሆይ፤ ምኞቴ ሁሉ በፊትህ ግልጽ ነው፤
ጭንቀቴም ከአንተ የተሰወረ አይደለም።

10 ልቤ በኀይል ይመታል፤ ጒልበት ከድቶኛል፤
የዐይኔም ብርሃን ጠፍቶአል።

11 ከቊስሌ የተነሣ ወዳጆቼም ባልንጀሮቼም ሸሹኝ፤
ጎረቤቶቼም ርቀው ቆሙ።

12 ሕይወቴን ለማጥፋት የሚሹ ወጥመድ ዘረጉብኝ፤
ሊጐዱኝ የሚፈልጉ ሊያጠፉኝ ዛቱ፤
ቀኑንም ሙሉ ተንኰል ይሸርባሉ።


13 እኔ ግን እንደማይሰማ ደንቈሮ፣
አፉንም መክፈት እንደማይችል ዲዳ ሆንሁ።

14 በእርግጥም ጆሮው እንደማይሰማ፣
አንደበቱም መልስ መስጠት እንደማይችል ሰው ሆንሁ።

15  እግዚአብሔር ሆይ፤ በተስፋ እጠብቅሃለሁ፤
ጌታ አምላኬ ሆይ፤ አንተ መልስ ትሰጠኛለህ።

16 እኔ፣ “ጠላቶቼ በእኔ ላይ ደስ አይበላቸው፤
እግሬም ሲንሸራተት፣ በላዬ አይኵራሩብኝ” ብያለሁና።


17 ልወድቅ ተቃርቤአለሁ፤
ከሥቃዬም ከቶ አልተላቀቅሁም።

18 በደሌን እናዘዛለሁ፤
ኀጢአቴም አውካኛለች።

19 ብርቱዎች ጠላቶቼ ብዙ ናቸው፤
ያለ ምክንያት የሚጠሉኝም ስፍር ቊጥር የላቸውም።

20 መልካሙን ስለ ተከተልሁ፣
በበጎ ፈንታ ክፉ የሚመልሱልኝ ጠሉኝ።


21  እግዚአብሔር ሆይ፤ አትተወኝ፤
አምላኬ ሆይ፤ ከእኔ አትራቅ።

22 ጌታዬ መድኅኔ ሆይ፤
እኔን ለመርዳት ፍጠን።
Copyright information for AmhNASV