Psalms 101
ትክክለኛ አስተዳደር
የዳዊት መዝሙር
1 ስለ ምሕረትና ስለ ፍትሕ እዘምራለሁ፤
እግዚአብሔር ሆይ፤ ለአንተ በምስጋና እቀኛለሁ።
2 እንከን የማይገኝባትን መንገድ አጥብቄ እይዛለሁ፤
አንተ ወደ እኔ የምትመጣው መቼ ነው?
በቤቴ ውስጥ፣
በንጹሕ ልብ እመላለሳለሁ።
3 በዐይኔ ፊት፣
ክፉ ነገር አላኖርም።
የከሓዲዎችን ሥራ እጠላለሁ፤
ከእኔም ጋር አይጣበቅም።
4 ጠማማ ልብ ከእኔ ይርቃል፤
ለክፋትም ዕውቅና አልሰጥም።
5 ባልንጀራውን በስውር የሚያማውን፣
አጠፋዋለሁ፤
ትዕቢተኛ ዐይንና ኵራተኛ ልብ ያለውን፣
እርሱን አልታገሠውም።
6 ከእኔ ጋር ይኖሩ ዘንድ፣
ዐይኖቼ በምድሪቱ ታማኞች ላይ ናቸው፤
በንጽሕና መንገድ የሚሄድ፣
እርሱ ያገለግለኛል።
7 አታላይ የሆነ ማንም ሰው፣
በቤቴ ውስጥ አይኖርም፤
ሐሰትን የሚናገር፣
በፊቴ ቀና ብሎ አይቆምም።
8 በምድሪቱ ላይ ያሉትን ክፉዎች ሁሉ፣
በየማለዳው አጠፋቸዋለሁ፤
ክፉ አድራጊዎችንም ሁሉ፣
ከእግዚአብሔር ከተማ እደመስሳቸዋለሁ።
Copyright information for
AmhNASV