Psalms 138
የምስጋና መዝሙር
የዳዊት መዝሙር
1 እግዚአብሔር ሆይ፤ በፍጹም ልቤ አመሰግንሃለሁ፤
በአማልክት ፊት በመዝሙር እወድስሃለሁ።
2 ወደ ቅዱስ መቅደስህ እሰግዳለሁ፤
ስለ ምሕረትህና ስለ ታማኝነትህ፣
ለስምህ ምስጋና አቀርባለሁ፤
ስምህንና ቃልህን፣
ከሁሉ በላይ ከፍ ከፍ አድርገሃልና።
3 በጠራሁህ ቀን መልስ ሰጠኸኝ፤
ነፍሴን በማደፋፈርም ብርቱ አደረግኸኝ።
4 እግዚአብሔር ሆይ፤ የአፍህን ቃል በሰሙ ጊዜ፣ የምድር ነገሥታት ሁሉ
ያመስግኑህ።
5 የእግዚአብሔር ክብር ታላቅ ነውና፣
ስለ እግዚአብሔር መንገድ ይዘምሩ።
6 እግዚአብሔር በከፍታ ስፍራ ቢሆንም፣ ዝቅ ያለውን ይመለከተዋል፤
ትዕቢተኛውን ከሩቅ ያውቀዋል።
7 በመከራ መካከል ብሄድም፣
አንተ ሕይወቴን ትጠብቃታለህ፤
በጠላቶቼ ቍጣ ላይ እጅህን ትዘረጋለህ፤
በቀኝ እጅህም ታድነኛለህ።
8 እግዚአብሔር በእኔ ላይ ያለውን ዐላማ ይፈጽማል፤
እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህ ለዘላለም ነው።
የእጅህንም ሥራ ቸል አትበል።
Copyright information for
AmhNASV