Psalms 146
ለረድኤት አምላክ ምስጋና
1 ሃሌ ሉያ። ▼
▼ አንዳንዶች ከ10 ጭምር እግዚአብሔር ይመስገን ይላሉ።
ነፍሴ ሆይ፤ እግዚአብሔርን ባርኪ።
2 በምኖርበት ዘመን ሁሉ እግዚአብሔርን
አመሰግናለሁ፤
በሕይወትም እስካለሁ ለአምላኬ እዘምራለሁ።
3በገዦች አትታመኑ፤ ማዳን በማይችሉ ሥጋ ለባሾችም አትመኩ።
4 መንፈሳቸው ትወጣለች፤ ወደ መሬታቸውም ይመለሳሉ፤
ያን ጊዜም ዕቅዳቸው እንዳልነበር ይሆናል።
5 ረዳቱ የያዕቆብ አምላክ የሆነ፣
ተስፋውንም በአምላኩ በእግዚአብሔር ላይ የጣለ ሰው ምስጉን ነው፤
6 እርሱ ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንም፣
በእነዚህም ውስጥ ያለውን ሁሉ የፈጠረ፣
ታማኝነቱንም ለዘላለም የሚጠብቅ ነው፤
7 ለተበደሉት የሚፈርድ፣
ለተራቡት ምግብን የሚሰጥ እርሱ ነው፤
እግዚአብሔር እስረኞችን ከእስራት ያወጣል፤
8 እግዚአብሔር የዕዉራንን ዐይን ያበራል፤
እግዚአብሔር የተዋረዱትን ከፍ ያደርጋል፤
እግዚአብሔር ጻድቃንን ይወዳል፤
9 እግዚአብሔር ስደተኞችን ይጠብቃል፤
ድኻ ዐደጎችንና መበለቶችን ይደግፋል፤
የክፉዎችን መንገድ ግን ያጠፋል።
10 እግዚአብሔር ለዘላለም ይነግሣል፤
ጽዮን ሆይ፤ አምላክሽ ለትውልድ ሁሉ ንጉሥ ነው።
ሃሌ ሉያ።
Copyright information for
AmhNASV