Psalms 34

የእግዚአብሔር ፍትሕ ውዳሴ

እንደ እብድ ሆኖ አቤሜሌክ ፊት በመቅረቡ ተባሮ በወጣ ጊዜ የዘመረው፤ የዳዊት መዝሙር


1  እግዚአብሔርን ሁል ጊዜ እባርከዋለሁ፤
ምስጋናውም ዘወትር ከአፌ አይለይም።

2 ነፍሴ  በእግዚአብሔር ተመካች፤
ትሑታንም ይህን ሰምተው ሐሤት ያደርጋሉ።

3 ኑና ከእኔ ጋር  እግዚአብሔርን አክብሩት፤
ስሙንም በአንድነት ከፍ ከፍ እናድርግ።


4  እግዚአብሔርን ፈለግሁት፤ እርሱም መለሰልኝ፤
ከፍርሀቴም ሁሉ አዳነኝ።

5 ወደ እርሱ የሚመለከቱ ያበራሉ፤
ፊታቸውም ከቶ አያፍርም።

6 ይህ ችግረኛ ጮኸ፤  እግዚአብሔርም ሰማው፤
ከመከራውም ሁሉ አዳነው።

7  እግዚአብሔርን በሚፈሩት ዙሪያ  የእግዚአብሔር መልአክ ይሰፍራል፤
ያድናቸዋልም።


8  እግዚአብሔር ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እዩ፤
እርሱን መጠጊያ የሚያደርግ ምንኛ ቡሩክ ነው!

9 እናንተ ቅዱሳኑ፤  እግዚአብሔርን ፍሩት፤
እርሱን የሚፈሩት አንዳች አያጡምና።

10 አንበሶች ሊያጡ፣ ሊራቡም ይችላሉ፤
 እግዚአብሔርን የሚሹ ግን መልካም ነገር አይጐድልባቸውም።

11 ልጆቼ ሆይ፣ ኑ፤ ስሙኝ፤
 እግዚአብሔርን መፍራት አስተምራችኋለሁ።

12 ሕይወትን የሚወድ፣
በጎውንም ያይ ዘንድ ዕድሜን የሚመኝ ማን ነው?

13 አንደበትህን ከክፉ ነገር ከልክል፤
ከንፈርህንም ከሽንገላ ጠብቅ።


14 ከክፉ ሽሽ፤ መልካሙንም አድርግ፤
ሰላምን ፈልጋት፤ ተከተላትም።

15  የእግዚአብሔር ዐይኖች ወደ ጻድቃን ናቸው፤
ጆሮዎቹም ለጩኸታቸው ክፍት ናቸው።

16 መታሰቢያቸውን ከምድር ለማጥፋት፣
 የእግዚአብሔር ፊት በክፉ አድራጊዎች ላይ ነው።


17 ጻድቃን ሲጮኹ፣  እግዚአብሔር ይሰማቸዋል፤
ከመከራቸውም ሁሉ ያድናቸዋል።

18  እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤
መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል።


19 የጻድቅ መከራው ብዙ ነው፤
 እግዚአብሔር ግን ከሁሉም ያድነዋል።

20 ዐጥንቶቹን ሁሉ ይጠብቃል፤
ከእነርሱም አንድ አይሰበርም።


21 ኀጢአተኞችን ክፋት ይገድላቸዋል፤
ጻድቃንን የሚጠሉ ይፈረድባቸዋል።

22  እግዚአብሔር የባሪያዎቹን ነፍስ ይቤዣል፤
እርሱንም መጠጊያ ያደረገ አይፈረድበትም።
Copyright information for AmhNASV