Psalms 75
ለመለኮታዊው ዳኛ የቀረበ ዝማሬ
ለመዘምራን አለቃ፤ “አታጥፋ” በሚለው ቅኝት የሚዜም፤ የአሳፍ መዝሙር ማሕሌት
1 አምላክ ሆይ፤ ምስጋና እናቀርብልሃለን፤
ስምህ ቅርብ ነውና ምስጋና እናቀርብልሃለን፤
ሰዎችም ስለ ድንቅ ሥራህ ይናገራሉ።
2 አንተም እንዲህ አልህ፤ “ለይቼ በወሰንኋት ሰዓት፣
በቅን የምፈርድ እኔ ነኝ።
3 ምድርና ሕዝቦቿ ሁሉ በሚናወጡበት ጊዜ፣
ምሰሶቿን አጽንቼ የምይዝ እኔ ነኝ።
ሴላ
4 እብሪተኛውን፣ ‘አትደንፋ’፤
ክፉውንም ‘ቀንድህን ከፍ አታድርግ እለዋለሁ፤
5 ቀንድህን ወደ ሰማይ አታንሣ፤
ዐንገትህንም መዝዘህ አትናገር።’ ”
6 ክብር ከምሥራቅ ወይም ከምዕራብ፣
ወይም ከምድረ በዳ አይመጣምና፤
7 ነገር ግን የሚፈርድ እግዚአብሔር ነው፤
እርሱ አንዱን ዝቅ፣ ሌላውን ከፍ ያደርጋል።
8 በእግዚአብሔር እጅ ጽዋ አለ፤
በሚገባ የተቀመመና ዐረፋ የሚወጣው የወይን ጠጅ ሞልቶበታል፤
ይህን ከውስጡ ወደ ውጭ ገለበጠው፤
የምድር ዐመፀኞችም አተላው ሳይቀር ይጨልጡታል።
9 እኔ ግን ይህን ለዘላለም ዐውጃለሁ፤
ለያዕቆብም አምላክ ዝማሬ አቀርባለሁ።
10 የክፉዎችን ሁሉ ቀንድ እሰብራለሁ፤
የጻድቃን ቀንድ ግን ከፍ ከፍ ይላል።
Copyright information for
AmhNASV