‏ Psalms 3

የመከራ ተቀባዩ የጧት ጸሎት

ዳዊት ከልጁ ከአቤሴሎም በሸሸ ጊዜ የዘመረው መዝሙር።

1 እግዚአብሔር ሆይ፤ ጠላቶቼ ምንኛ በዙ!
ስንቱስ በእኔ ላይ ተነሣ!
2ብዙዎች ነፍሴን፣ “እግዚአብሔር
አይታደግሽም” አሏት። ሴላ ▼
▼በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ በተደጋጋሚ የሚገኝ ሲሆን፣ የቃሉ ትርጕም በትክክል አይታወቅም፤ የሙዚቃ ምልክት ሳይሆን አይቀርም


3 እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ግን ዙሪያዬን
የምትከልል ጋሻ ነህ፤
ክብሬንና ራሴንም ቀና ቀና
የምታደርግ አንተ ነህ። ▼
▼ወይም እግዚአብሔር… ወደ ላይ የምታነሣ ክብሬ ሆይ

4ወደ እግዚአብሔር ድምፄን ከፍ አድርጌ እጮሃለሁ፤
እርሱም ከተቀደሰ ተራራው ይመልስልኛል። ሴላ

5እተኛለሁ፤ አንቀላፋለሁ፤
እግዚአብሔር ደግፎ ይዞኛልና እነቃለሁ።
6በየአቅጣጫው የከበበኝን፣
አእላፍ ሕዝብ አልፈራም።

7 እግዚአብሔር ሆይ ተነሥ!
አምላኬ ሆይ፤ ታደገኝ፤
የጠላቶቼን ሁሉ መንጋጋ ትመታለህ፤
የክፉዎችንም ጥርስ ትሰባብራለህ።

8ማዳን የእግዚአብሔር ነው፤
በረከትህ በሕዝብህ ላይ ይሁን። ሴላ
Copyright information for AmhNASV