1 Chronicles 16
1ከዚያም የእግዚአብሔርን ታቦት አምጥተው ዳዊት በተከለለት ድንኳን ውስጥ አኖሩት፤ የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕትም ▼▼በዚህና በቍጥር 2 ላይ በትውፊት የሰላም መሥዋዕት ይባላል።
በእግዚአብሔር ፊት አቀረቡ። 2ዳዊት የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የኅብረቱን መሥዋዕት ከሠዋ በኋላ፣ ሕዝቡን በእግዚአብሔር ስም ባረከ። 3ከዚያም ለእስራኤል ሁሉ ለወንዱም ለሴቱም አንዳንድ ሙልሙል ዳቦ፣ አንዳንድ ጥፍጥፍ ተምር፣ ሙዳ ሙዳ ሥጋና አንዳንድ ጥፍጥፍ ዘቢብ ሰጠ። 4 በእግዚአብሔር ታቦት ፊት እንዲያገለግሉና ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ልመና፣ ምስጋናና ውዳሴ እንዲያቀርቡ ከሌዋውያን ሰዎች ሾመ፤ 5አለቃው አሳፍ ነበረ፤ ከእርሱ ቀጥሎ ዘካርያስ ሁለተኛ ሆኖ ተሾመ፤ ከዚያም ይዒኤል፣ ሰሚራሞት፣ ይሒኤል፣ መቲትያ፣ ኤልያብ፣ በናያስ፣ ዖቤድኤዶም፣ ይዒኤል ተሾሙ፤ እነርሱም በመሰንቆና በበገና ይዘምሩ ነበር፤ አሳፍ ደግሞ ጸናጽል የሚጸነጽል ሆኖ ተመደበ። 6እንዲሁም ካህናቱ በናያስና የሕዚኤል ዘወትር በእግዚአብሔር የኪዳኑ ታቦት ፊት መለከት እንዲነፉ ተመደቡ።
የዳዊት የምስጋና መዝሙር
16፥8-22 ተጓ ምብ – መዝ 105፥1-15 16፥23-33 ተጓ ምብ – መዝ 96፥1-13 16፥34-36 ተጓ ምብ – መዝ 106፥1፡47-48 7በዚያም ቀን ዳዊት በመጀመሪያ ለአሳፍና ለሥራ ጓደኞቹ ይህን የእግዚአብሔር ምስጋና መዝሙር ሰጠ፤8 ለእግዚአብሔር ምስጋና አቅርቡ፤ ስሙንም ጥሩ፤
ለአሕዛብ ያደረገውን ሁሉ ንገሩ፤
9ዘምሩለት፤ ውዳሴም አቅርቡለት፤
ድንቅ ሥራውን ሁሉ ንገሩ፤
10በቅዱስ ስሙ ተጓደዱ፤
እግዚአብሔርን የሚፈልጉ ሁሉ፣ ልባቸው ሐሤት ያድርግ።
11ወደ እግዚአብሔርና ወደ ኀይሉ ተመልከቱ፤
ዘወትር ፊቱን ፈልጉ።
12ያደረጋቸውን ድንቅ ሥራዎች፣
ታምራቱንና የሰጠውንም ፍርድ አስታውሱ፤
13እናንተ የባሪያው የእስራኤል ዘሮች፣
እናንተ የተመረጣችሁ የያዕቆብ ልጆች።
14እርሱ እግዚአብሔር አምላካችን ነው፤
ፍርዱም በምድር ሁሉ ላይ ነው፤
15ኪዳኑን እስከ ዘላለም፣
ያዘዘውንም ቃል እስከ ሺሕ ትውልድ ያስባል።
16ከአብርሃም ጋር የገባውን ቃል ኪዳን፣
ለይስሐቅ የማለውን መሐላ።
17ይህንም ለያዕቆብ ሥርዐት አድርጎ አጸና፤
ለእስራኤልም የዘላለም ኪዳን አደረገ፤
18እንዲህ ሲል፣ “የምትወርሰው ርስት እንዲሆን፣
የከነዓንን ምድር ለአንተ እሰጣለሁ።”
19ቍጥራቸው ገና ጥቂት ሳለ፣
በርግጥ ጥቂትና መጻተኞች ሳሉ፣
20ከአንዱ ሕዝብ ወደ ሌላው ሕዝብ፣
ከአንዱም መንግሥት ወደ ሌላው መንግሥት ተንከራተቱ።
21ማንም እንዲጨቍናቸው አልፈቀደም፤
ስለ እነርሱም ነገሥታትን ገሠጸ፤
22እንዲህ ሲል፤ “የቀባኋቸውን አትንኩ፤
በነቢያቴ ላይ ክፉ አታድርጉ።”
23ምድር ሁሉ ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤
ማዳኑንም ዕለት ዕለት ዐውጁ።
24ክብሩን ለአሕዛብ ተናገሩ፤
ድንቅ ሥራዎቹን ለሕዝቦች ሁሉ ንገሩ።
25 እግዚአብሔር ታላቅ ነው፤ ምስጋናውም ብዙ ነው፤
ከአማልክትም ሁሉ በላይ ሊፈራ የሚገባው ነው።
26የአሕዛብ ሁሉ አማልክት ጣዖታት ናቸው፤
እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ።
27በፊቱ ክብርና ሞገስ አለ፤
ብርታትና ደስታም በማደሪያው ስፍራ።
28የአሕዛብ ወገኖች ለእግዚአብሔር ስጡ፤
ክብርና ኀይልን ለእግዚአብሔር አምጡ።
29ለስሙ የሚገባውን ክብር ለእግዚአብሔር ስጡ፤
መባ ይዛችሁ በፊቱ ቅረቡ፤
በቅድስናውም ክብር ለእግዚአብሔር ▼
▼ወይም፣ ከክብሩ ጋር ለእግዚአብሔር
ስገዱ።30ምድር ሁሉ በፊቱ ትንቀጥቀጥ፤
ዓለም በጽኑ ተመሥርታለች፤ አትናወጥምም።
31ሰማያት ደስ ይበላቸው፤ ምድር ሐሤት ታድርግ፤
በአሕዛብም መካከል፤ “እግዚአብሔር ነገሠ!” ይበሉ።
32ባሕርና በውስጧ ያለው ሁሉ ይናወጥ፤
ሜዳዎችና በእርሷ ላይ ያሉ ሁሉ ሐሤት ያድርጉ።
33ያን ጊዜ የዱር ዛፎች በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይላቸዋል፤
በደስታ ይዘምራሉ፤
በምድረ በዳ ላይ ሊፈርድ ይመጣልና።
34ቸር ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ፤
ፍቅሩም ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።
35“አዳኛችን እግዚአብሔር ሆይ ታደገን፤
ለቅዱስ ስምህ ምስጋና እንድናቀርብ፣ በምስጋናህም እንድንከብር ሰብስበን፤
ከአሕዛብም መካከል ታደገን”
ብላችሁ ጩኹ።
36ከዘላለም እስከ ዘላለም፣
ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን።
ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ፣ “አሜን፤ እግዚአብሔር ይመስገን” አሉ።
37ዳዊትም ለእያንዳንዱ ቀን በተመደበው መሠረት፣ ዘወትር እንዲያገለግሉ አሳፍንና የሥራ ባልደረቦቹን በዚያው በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ፊት ተዋቸው። 38እንዲሁም ዖቤድኤዶምና ስድሳ ስምንቱ የሥራ ባልደረቦቹ አብረዋቸው እንዲያገለግሉ በዚያው ተዋቸው። የኤዶታም ልጅ ዖቤድኤዶምና ሖሳ የቅጥሩ በር ጠባቂዎች ሆኑ።
39ዳዊት ካህኑን ሳዶቅንና የሥራ ባልደረቦቹን ካህናት በገባዖን ከፍተኛ ቦታ ላይ በሚገኘው በእግዚአብሔር ድንኳን ተዋቸው፤ 40የተዋቸውም ለእስራኤል በተሰጠው ትእዛዝ መሠረት፣ በእግዚአብሔር ሕግ እንደ ተጻፈው ሁሉ፣ በመሠዊያው ላይ የሚቀርበውን የሚቃጠል መሥዋዕት ጧትና ማታ በየጊዜው እንዲያቀርቡ ነው። 41እንዲሁም “ፍቅሩ ለዘላለም ነውና” እያሉ ለእግዚአብሔር ምስጋና እንዲያቀርቡ ኤማንና ኤዶታም እንዲሁም ተመርጠውና ስማቸው ተመዝግቦ የተመደቡ ሌሎችም አብረዋቸው ነበሩ። 42ድምፀ መለከቱንና ጸናጽሉን ለማሰማት፣ ደግሞም መንፈሳዊ መዝሙር ሲዘመር ለሚጠቀሙባቸው ሌሎች መሣሪያዎች ኀላፊዎቹ ኤማንና ኤዶታም ነበሩ፤ የኤዶታምም ልጆች በሩን እንዲጠብቁ ተመድበው ነበር።
43ከዚያም ሕዝቡ ተነሣ፤ እያንዳንዱም ወደየቤቱ ሄደ። ዳዊትም ቤተ ሰቡን ለመባረክ ወደ ቤቱ ተመለሰ።
Copyright information for
AmhNASV