‏ 1 Kings 6

ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን መሥራት ጀመረ

6፥1-29 ተጓ ምብ – 2ዜና 3፥1-14 1እስራኤላውያን ከግብፅ በወጡ በአራት መቶ ሰማንያ
ዕብራይስጡ ከዚህ ጋር ይስማማል፤ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም አራት መቶ አርባ ይላሉ።
ዓመት፣ ሰሎሞን በእስራኤል ላይ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፣ ዚፍ በተባለው በሁለተኛው ወር ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ መሥራት ጀመረ።

2ንጉሥ ሰሎሞን ለእግዚአብሔር የሠራው ቤተ መቅደስ ርዝመቱ ስድሳ ክንድ፣ ወርዱ ሃያ ክንድ፣ ቁመቱ ሠላሳ ክንድ
ርዝመቱ 27 ሜትር፣ ወርዱ 9 ሜትር እንዲሁም ቁመቱ 13.5 ሜትር ያህል ነው።
ነበር።
3በቤተ መቅደሱ ዋነኛ አዳራሽ ፊት ለፊት ያለው በረንዳ ወርዱ እንደ ቤተ መቅደሱ ወርድ ሁሉ ሃያ ክንድ
9 ሜትር ያህል ነው።
ሲሆን፣ ርዝመቱ ዐሥር ክንድ
4.5 ሜትር ያህል ነው።
ወደ ውጭ የወጣ ነበር።
4ለቤተ መቅደሱም ባለ ዐይነ ርግብ መስኮቶች አበጀ። 5በዋናው ቤተ መቅደስና በቅድስተ ቅዱሳኑ ግድግዳ ዙሪያ ልዩ ክፍሎች ያሉት ተቀጥላ ግንብ ሠራ። 6የምድር ቤቱ ወርድ አምስት ክንድ፣
በዚህ እንዲሁም በ10 እና 24 ላይ 2.3 ሜትር ያህል ነው።
የመካከለኛው ፎቅ ስድስት ክንድ፣
2.7 ሜትር ያህል ነው።
የሦስተኛው ፎቅ ሰባት ክንድ
3.1 ሜትር ያህል ነው።
ነበር፤ የቤተ መቅደሱን ግድግዳ ዘልቆ እንዳይገባም፣ ከቤተ መቅደሱ ግንብ ውጭ ዙሪያውን እርከኖች አደረገ።

7ቤተ መቅደሱ የተሠራው እዚያው ድንጋዩ ተቈፍሮ ከወጣበት ቦታ በተዘጋጀ ድንጋይ በመሆኑ የመራጃ፣ የመሮ ወይም የሌላ ብረት ነክ መሣሪያ ድምፅ በቤተ መቅደሱ አካባቢ አልተሰማም ነበር።

8የምድር ቤቱ
የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም ከዚህ ጋር ይስማማል፤ ዕብራይስጡ ግን የመካከለኛው ደርብ ይላሉ።
መግቢያ በስተ ደቡብ በኩል ባለው የቤተ መቅደሱ ጐን ሲሆን፣ ወደ መካከለኛውና ከዚያም ወደ መጨረሻው ፎቅ የሚያስወጣ ደረጃ ነበረው።
9ቤተ መቅደሱንም በዚሁ ሁኔታ ሠርቶ ጨረሰ፤ ለጣራው ተሸካሚ አደረገለት፤ በዝግባ ሳንቃም ከደነው። 10በቤተ መቅደሱም ዙሪያ በሙሉ፣ ቁመታቸው አምስት አምስት ክንድ የሆነ ክፍሎች ሠራ፤ እነዚህንም ከቤተ መቅደሱ ጋር በዝግባ አግዳሚ ዕንጨቶች አያያዛቸው።

11 የእግዚአብሔርም ቃል እንዲህ ሲል ወደ ሰሎሞን መጣ፤ 12“ስለምትሠራው ስለዚህ ቤተ መቅደስ ሥርዐቴን ብትከተል፣ ፍርዴን በተግባር ብትገልጸው፣ ትእዛዞቼን ብትጠብቅና ብትመላለስባቸው ለአባትህ ለዳዊት የሰጠሁትን ተስፋ በአንተ እፈጽመዋለሁ፤ 13በእስራኤላውያን መካከል እኖራለሁ፤ ሕዝቤን እስራኤልንም አልተወውም።”

14ስለዚህ ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን ሠርቶ ፈጸመ፤ 15የውስጡን ግድግዳ ከቤተ መቅደሱ ወለል እስከ ጣራው ድረስ በዝግባ ሳንቃ ለበጠ፤ የቤተ መቅደሱንም ወለል የጥድ ሳንቃ አለበሰው። 16በቤተ መቅደሱም ውስጥ በስተ ኋላ በኩል፣ ሃያውን ክንድ ቅድስተ ቅዱሳን እንዲሆን፣ ከወለሉ አንሥቶ እስከ ጣራው ድረስ በዝግባ ሳንቃዎች ጋረደው፤ 17በቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ለፊት ያለው ዋና አዳራሽ ርዝመቱ አርባ ክንድ
18 ሜትር ያህል ነው።
ነበር።
18የቤተ መቅደሱም፣ ውስጡ በሙሉ በዝግባ የተለበጠ ሲሆን፣ ይህም በእንቡጥ አበቦችና በፈኩ አበቦች ቅርጽ የተጌጠ ነበር፤ በሙሉ ዝግባ እንጂ የሚታይ ድንጋይ አልነበረም።

19በቤተ መቅደሱም ውስጠኛ ክፍል የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት የሚቀመጥበትን ቅድስተ ቅዱሳን ሠራ። 20ቅድስተ ቅዱሳኑም ርዝመቱ ሃያ ክንድ፣ ወርዱ ሃያ ክንድ፣ ቁመቱም ሃያ ክንድ
ርዝመቱ፣ ወርዱና ቁመቱ 9 ሜትር ያህል ነው።
ነበር፤ ውስጡን በንጹሕ ወርቅ ለበጠው፤ ከዝግባ የተሠራውንም መሠዊያ በወርቅ ለበጠው።
21ሰሎሞንም ቤተ መቅደሱን በውስጥ በኩል በንጹሕ ወርቅ ለበጠው፤ በወርቅ በተለበጠው ቅድስተ ቅዱሳን ፊት ለፊትም የወርቅ ሰንሰለቶች ዘረጋ። 22ስለዚህ ውስጡን በሙሉ በወርቅ ለበጠው፤ በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ያለውን መሠዊያም እንደዚሁ በወርቅ ለበጠው። 23በቅድስተ ቅዱሳኑም ውስጥ ቁመታቸው ዐሥር ክንድ
4.5 ሜትር ያህል ነው።
የሆነ ሁለት የኪሩቤል ቅርጽ ከወይራ ዕንጨት ሠራ፤
24የአንደኛው ኪሩብ አንዱ ክንፍ አምስት ክንድ ሲሆን፣ ሌላውም ክንፉ እንደዚሁ አምስት ክንድ ነበር፤ ይህም ከአንዱ ክንፍ ጫፍ እስከ ሌላው ክንፍ ጫፍ ዐሥር ክንድ ማለት ነው። 25የሁለተኛውም ኪሩብ ክንፍ እንደዚሁ ዐሥር ክንድ ሆነ፤ ሁለቱ ኪሩቤል በመጠንና በቅርጽ አንድ ዐይነት ነበሩና። 26የእያንዳንዱም ኪሩብ ቁመት ዐሥር ክንድ ነበር። 27ክንፎቻቸው እንደ ተዘረጋ፣ ኪሩቤልን ወስዶ በቅድስተ ቅዱሳኑ አኖራቸው፤ የአንዱ ኪሩብ ክንፍ አንዱን ግድግዳ ሲነካ፣ የሌላው ኪሩብ ክንፍ ደግሞ ሌላውን ግድግዳ ይነካ ነበር፤ ሌሎቹ ክንፎቻቸውም በቅድስተ ቅዱሳኑ መካከል እርስ በርሳቸው ይነካኩ ነበር። 28ኪሩቤልንም በወርቅ ለበጣቸው።

29በመቅደሱ ግድግዳ ዙሪያ ላይ ሁሉ በውስጥም በውጭም ኪሩቤልን፣ ከዘንባባ ዛፎችና ከፈነዱ አበቦች ጋር ቀረጸ። 30እንዲሁም የቅድስተ ቅዱሳኑንና የመቅደሱን ወለል በሙሉ በወርቅ ለበጠ።

31ለቅድስተ ቅዱሳኑም መግቢያ የወይራ ዕንጨት ደጃፎች ሠራ፤ መቃኖቻቸውንና መድረኮቻቸውን ባለ አምስት ማእዘን አደረገ። 32በሁለቱ የወይራ ዕንጨት መዝጊያዎችም ላይ ኪሩቤልን፣ የዘንባባ ዛፎችንና የፈነዱ አበቦችን ቀረጸ፤ በወርቅም ለበጣቸው። 33እንዲሁም ለዋናው አዳራሽ መግቢያ ባለ አራት ማእዘን የወይራ ዕንጨት መቃን ሠራ፤ 34እያንዳንዳቸው በማጠፊያ የተያያዙ ሁለት ሁለት ሳንቃዎች ያሏቸው ሁለት መዝጊያዎች አበጀ። 35ኪሩቤልን፣ የዘንባባ ዛፎችንና የፈኩ አበቦችንም ቀረጸባቸው፤ ቅርጹን ሠራ፤ ጥሩ አድርጎም በወርቅ ለበጠው።

36የውስጠኛውን አደባባይ በሦስት ረድፍ ጥርብ ድንጋይና በአንድ ረድፍ የዝግባ ሳንቃ ሠራው።

37የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም በአራተኛው ዓመት ዚፍ በተባለው ወር መሠረቱ ተጣለ፤ 38በዐሥራ አንደኛው ዓመት ቡል በተባለውም በስምንተኛው ወር ቤተ መቅደሱ በዝርዝር ጥናቱ መሠረት እንደ ታቀደው ተፈጸመ፤ ሠርቶ የጨረሰውም በሰባት ዓመት ጊዜ ውስጥ ነበር።

Copyright information for AmhNASV