1 Samuel 15
እግዚአብሔር የሳኦልን ንጉሥነት መናቁ
1ሳሙኤል ሳኦልን እንዲህ አለው፤ “በሕዝቡ በእስራኤል ላይ ቀብቼ እንዳነግሥህ፣ እግዚአብሔር የላከው እኔን ነው፤ ስለዚህ ከእግዚአብሔር የመጣውን መልእክት አድምጥ። 2የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እስራኤል ከግብፅ በወጣ ጊዜ፣ አማሌቃውያን በመንገድ ላይ ስለ ተቃወሙት እቀጣቸዋለሁ። 3አሁንም ሂድ፤ አማሌቃውያንን ውጋ፤ ያላቸውንም ሁሉ ፈጽመህ አጥፋ፤ አንዱንም አታስቀር፤ ወንዱንና ሴቱን፣ ልጁንና ሕፃኑን፣ የቀንድ ከብቱንና በጉን፣ ግመሉንና አህያውን ግደል።’ ” ▼▼በዚህም ሆነ በቍጥር 8፡9፡15፡18፡20 እና 21 ላይ የዕብራይስጡ ቃል አንድን ሰው ወይም ነገር ሙሉ በሙሉ በማጥፋት ለእግዚአብሔር መስጠትን የሚያሳይ ነው።
4ስለዚህ ሳኦል ሰዎቹን ጥላኢም በተባለ ቦታ ሰብስቦ ቈጠራቸው፤ እነርሱም ሁለት መቶ ሺሕ እግረኛ ወታደሮችና ከይሁዳም ዐሥር ሺሕ ሰዎች ነበሩ፤ 5ሳኦልም ወደ አማሌቅ ከተማ ሄዶ በአንዲት ሸለቆ ውስጥ አደፈጠ። 6እርሱም፣ ቄናውያንን፣ “ከእነርሱ ጋር እንዳላጠፋችሁ ከአማሌቃውያን ራቁ፤ ተለዩአቸውም፤ እስራኤላውያን ከግብፅ ምድር በወጡ ጊዜ፣ ቸርነት አድርጋችሁላቸዋልና” አላቸው። ስለዚህ ቄናውያን ከአማሌቃውያን ተለዩ።
7ከዚያም ሳኦል አማሌቃውያንን ከኤውላጥ አንሥቶ በምሥራቅ ግብፅ እስካለው እስከ ሱር ድረስ ወጋቸው። 8የአማሌቃውያንን ንጉሥ አጋግን ከነሕይወቱ ማረከው፤ ሕዝቡን ሁሉ በሰይፍ ስለት ፈጽሞ አጠፋቸው። 9ነገር ግን ሳኦልና ሰራዊቱ አጋግን፣ ምርጥ ምርጡን በግና የቀንድ ከብት፣ የሰባውን ጥጃና ▼
▼ወይም ያደገ ጥጃ የዚህ ሐረግ የዕብራይስጡ ትርጕም በትክክል አይታወቅም።
ጠቦት፣ መልካም የሆነውን ሁሉ ሳይገድሉ ተውት። እነዚህን ፈጽመው ለማጥፋት ፈቃደኞች አልነበሩም፤ ነገር ግን የተናቀውንና የማይጠቅመውን ሁሉ አጠፉ። 10ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ ሳሙኤል መጣ፤ 11“ሳኦልን በማንገሤ ተጸጽቻለሁ፤ እኔን ከመከተል ተመልሷልና፣ ትእዛዜንም አልፈጸመምና።” ሳሙኤልም እጅግ ተጨንቆ፣ ሌሊቱን ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ።
12ሳሙኤልም ጧት ተነሥቶ በማለዳ ሳኦልን ለመገናኘት ሄደ፤ ነገር ግን፣ “ሳኦል ወደ ቀርሜሎስ ሄዷል፤ ለራሱ ክብር የመታሰቢያ ሐውልት በዚያ ካቆመ በኋላ ተመልሶ ወደ ጌልገላ ወርዷል” ተብሎ ተነገረው።
13ሳሙኤል ባገኘው ጊዜ ሳኦል፣ “እግዚአብሔር ይባርክህ፤ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ፈጽሜአለሁ” አለው።
14ሳሙኤል ግን፣ “ታዲያ ይህ በጆሮዬ የምሰማው የበጎች ጩኸትና የበሬዎች ግሣት ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀ።
15ሳኦልም፣ “ሰራዊቱ ከአማሌቃውያን ማርከው ያመጧቸው ናቸው፤ ምርጥ ምርጦቹ በጎችና በሬዎች ለእግዚአብሔር ለአምላክህ መሥዋዕት እንዲሆኑ ሳይገድሉ የተዉአቸው ናቸው፤ የቀሩትን ግን በሙሉ አጥፍተናል” ብሎ መለሰ።
16ሳሙኤልም ሳኦልን፣ “ስማ! ትናንት ማታ እግዚአብሔር የነገረኝን ልንገርህ?” አለው።
ሳኦልም፣ “ንገረኝ” ሲል መለሰለት።
17ሳሙኤልም እንዲህ አለው፤ “በዐይንህ ፊት ታናሽ የነበርህ ብትሆንም፣ የእስራኤል ነገዶች መሪ ሆነህ የለምን? እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ቀብቶ አንግሦሃል። 18እግዚአብሔርም፣ ‘ሄደህ እነዚያን ኀጢአተኞቹን አማሌቃውያንን ፈጽመህ አጥፋቸው፤ ጨርሰህ እስክታጠፋቸውም ድረስ ውጋቸው’ ብሎ ልኮህ ነበር። 19ታዲያ እግዚአብሔርን ለምን አልታዘዝህም? ለምርኮውስ ተስገብግበህ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆነውን ነገር ለምን አደረግህ?”
20ሳኦልም መልሶ እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔርን ታዝዣለሁ፤ እግዚአብሔር በላከኝ መሠረት ሄጃለሁ፤ አማሌቃውያንን በሙሉ አጥፍቼ ንጉሣቸውን አጋግን አምጥቻለሁ። 21ሰራዊቱ ግን ከምርኮው ለእግዚአብሔር ከተለዩት መካከል፣ ምርጥ ምርጡን በግና በሬ፣ በጌልገላ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ይሠዉ ዘንድ ወስደዋል።”
22ሳሙኤልም እንዲህ አለ፤
“ለእግዚአብሔር ቃል በመታዘዝ ደስ የሚለውን ያህል፣ እግዚአብሔር፣
በሚቃጠል ቍርባንና መሥዋዕት ደስ ይለዋልን?
እነሆ! መታዘዝ ከመሥዋዕት፣
ማዳመጥም ከአውራ በግ ሥብ ይበልጣል።
23ዐመፅ እንደ ጥንቈላ ያለ ኀጢአት፣
እልኸኝነትም እንደ ጣዖት አምልኮ ያለ ክፉ ነገር ነው። አንተ የእግዚአብሔርን ቃል ስለ ናቅህ፣ እርሱም ንጉሥ እንዳትሆን ንቆሃል።”
24ከዚያም ሳኦል ሳሙኤልን እንዲህ አለው፤ “ኀጢአት ሠርቻለሁ፤ የእግዚአብሔርን ትእዛዝና የአንተን መመሪያ ጥሻለሁ፤ ሕዝቡን ፈርቼ ስለ ነበር፣ የጠየቁኝን ታዝዣለሁ። 25አሁንም፣ ኀጢአቴን ይቅር እንድትለኝ፣ ለእግዚአብሔርም እሰግድ ዘንድ አብረኸኝ እንድትመለስ እለምንሃለሁ።”
26ሳሙኤል ግን፣ “ከአንተ ጋር አልመለስም፤ አንተ የእግዚአብሔርን ቃል ንቀሃል፤ እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንዳትሆን ንቆሃል” አለው።
27ሳሙኤል ለመሄድ ዘወር ባለ ጊዜ፣ ሳኦል የልብሱን ጫፍ ያዘ፤ ተቀደደም። 28ሳሙኤልም እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር የእስራኤልን መንግሥት ዛሬ ከአንተ ቀዶታል፤ ከአንተም ለሚሻል ለጎረቤትህ አሳልፎ ሰጥቶታል። 29የእስራኤል ክብር የሆነው እግዚአብሔር አይዋሽም፤ አይጸጸትምም፤ እርሱ ይጸጸት ዘንድ ሰው አይደለምና።”
30ሳኦልም መልሶ፣ “ኀጢአት ሠርቻለሁ፤ ነገር ግን በሕዝቤ አለቆች ፊትና በእስራኤል ፊት አክብረኝ፤ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር እሰግድ ዘንድ እባክህ አብረኸኝ ተመለስ” አለው። 31ስለዚህ ሳሙኤል አብሮት ተመለሰ፤ ሳኦልም ለእግዚአብሔር ሰገደ።
32ከዚያም ሳሙኤል፣ “የአማሌቃውያንን ንጉሥ አጋግን አምጡልኝ” አለ።
አጋግም፣ “በውኑ ሞት እንዲህ መራራ ነውን?” በማለት እየተንቀጠቀጠ መጣ።
33ሳሙኤልም፣
“ሰይፍህ ሴቶችን ልጅ አልባ እንዳደረገቻቸው፣
እናትህም በሴቶች መካከል ልጅ አልባ ትሆናለች”
ሲል አጋግን ጌልገላ ላይ በእግዚአብሔር ፊት ቈራረጠው።
34ከዚያም ሳሙኤል ወደ አርማቴም ሄደ። ሳኦል ግን ወደ ቤቱ ወደ ሳኦል ጊብዓ ወጣ። 35ሳሙኤል ለሳኦል ቢያለቅስለትም እንኳ እስከ ሞተበት ዕለት ድረስ ዳግመኛ ሊያየው አልሄደም፤ እግዚአብሔርም ሳኦልን በእስራኤል ላይ በማንገሡ ተጸጸተ።
Copyright information for
AmhNASV