2 Chronicles 23
1በሰባተኛው ዓመት ዮዳሄ በረታ፤ የመቶ አለቆች ከሆኑት ከይሮሐም ልጅ ከዓዛርያስ፣ ከይሆሐናን ልጅ ከይስማኤል፣ ከዖቤድ ልጅ ከዓዛርያስ፣ ከዓዳያ ልጅ ከማዕሤያ፣ ከዝክሪ ልጅ ከኤሊሳፋጥ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። 2እነርሱም ወደ መላው ይሁዳ ሄደው፣ ሌዋውያንንና የእስራኤል ቤት አለቆችን ከየከተማው ሁሉ ሰበሰቡ። ወደ ኢየሩሳሌም በመጡ ጊዜም፣ 3ጉባኤው ሁሉ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ ከንጉሡ ጋር ቃል ኪዳን አደረጉ።ዮዳሄም እንዲህ አላቸው፤ “እግዚአብሔር ለዳዊት ዘር በሰጠው ተስፋ መሠረት እነሆ፤ የንጉሡ ልጅ ይነግሣል። 4እንግዲህ እናንተ የምታደርጉት ይህ ነው፤ በሰንበት ዕለት ተረኛ ከሆናችሁት ከእናንተ ከካህናቱና ከሌዋውያኑ አንድ ሦስተኛው በሮቹን ጠብቁ፤ 5አንድ ሦስተኛው ቤተ መንግሥቱን፣ አንድ ሦስተኛው ‘የመሠረት ቅጽር በር’ የተባለውን ጠብቁ፤ የቀሩት ሰዎች በሙሉ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አደባባይ ይሁኑ። 6ተረኛ ከሆኑት ካህናትና ሌዋውያን በቀር ማንም ሰው ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አይግባ፤ እነርሱ የተቀደሱ ስለሆኑ ይግቡ፤ የቀሩት ሰዎች በሙሉ ግን፣ ወደ ቤተ መቅደሱ እንዳይገቡ እግዚአብሔር ያዘዘውን ይጠብቁ ▼
▼ወይም አይግባ የሚለውን የእግዚአብሔር ትእዛዝ ይጠብቁ
። 7ሌዋውያኑም የጦር መሣሪያቸውን በእጃቸው ይዘው በንጉሡ ዙሪያ ይቁሙ፤ ወደ ቤተ መቅደሱ የሚገባ ማንኛውም ሰው ይገደል፤ ንጉሡ በሚሄድበትም ቦታ ሁሉ አብረውት ይሁኑ።” 8ሌዋውያኑና ይሁዳ ሁሉ ልክ ካህኑ ዮዳሄ እንዳዘዘው አደረጉ፤ ካህኑ ዮዳሄ ከጥበቃ ክፍሎች የትኛውንም አላሰናበተም ነበርና፣ እያንዳንዱ በሰንበት ቀን በሥራ ላይ የሚሰማሩትንና ከሥራ የሚወጡትን የራሱን ሰዎች ወሰደ፤ 9ከዚያም በቤተ መቅደሱ የነበሩትን የንጉሥ ዳዊት ጦሮች፣ ታላላቅና ታናናሽ ጋሻዎች ለመቶ አለቆቹ ሰጣቸው። 10ሰዎቹም ሁሉ እያንዳንዳቸው መሣሪያቸውን በእጃቸው እንደ ያዙ ከቤተ መቅደሱ ደቡብ አንሥቶ እስከ ሰሜን ድረስ በመሠዊያውና በቤተ መቅደሱ አጠገብ በንጉሡ ዙሪያ እንዲቆሙ አደረገ።
11ዮዳሄና ወንዶች ልጆቹ የንጉሡን ልጅ አምጥተው ዘውድ ጫኑለት፤ የኪዳኑንም መጽሐፍ ሰጥተውት አነገሡት፤ ቀብተውትም፣ “ንጉሡ ለዘላለም ይኑር!” እያሉ ጮኹ።
12ጎቶልያም የሚሯሯጠውንና ደስታውን ለንጉሡ የሚገልጠውን ሕዝብ ሁካታ ስትሰማ፣ ሕዝቡ ወዳለበት ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሄደች። 13ንጉሡ በመግቢያው ላይ ባለው በዐምዱ አጠገብ ቆሞ አየች፣ የጦር መኮንኖችና መለከት ነፊዎችም በንጉሡ አጠገቡ ነበሩ፤ የምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ ይደሰቱ፣ መለከትም ይነፉ ነበር፤ መዘምራንም በዜማ ዕቃ ታጅበው የበዓሉን ዝማሬ ይመሩ ነበር፤ ጎቶልያም ልብሷን ቀድዳ፣ “ይህ ዐመፅ ነው! ይህ ዐመፅ ነው!” ብላ ጮኸች።
14ካህኑ ዮዳሄም የወታደር አዛዥ ወደ ሆኑት ወደ መቶ አለቆቹ፣ “በሰልፉ መካከል አውጥታችሁ አምጧት ▼
▼ወይም ከቅጥሩ ውስጥ አውጥታችሁ አምጧት
፤ የሚከተላት ካለም በሰይፍ ግደሉት” ሲል ላከባቸው። ካህኑም፣ “በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አትግደሏት” ብሎ ነበርና። 15እርሷም በቤተ መንግሥቱ ግቢ የፈረስ መግቢያ በር ወደ ተባለው ቦታ እንደ ደረሰች ያዟት፤ በዚያም ገደሏት። 16ዮዳሄም ራሱ፣ ሕዝቡና ንጉሡ የእግዚአብሔር ሕዝብ እንደሚሆኑ ቃል ኪዳን ገባ ▼። 17ከዚህ በኋላ ሕዝቡ በሙሉ ሄዶ የበኣልን ቤተ ጣዖት አፈረሰው፤ መሠዊያዎቹንና ጣዖታቱን አደቀቀ፤ የበኣልን ካህን ማታንንም በመሠዊያዎቹ ፊት ለፊት ገደሉት። 18ዮዳሄ በሙሴ ሕግ እንደ ተጻፈውና ዳዊትም እንዳዘዘው፣ በደስታና በመዝሙር የሚቃጠለውን የእግዚአብሔርን መሥዋዕት እንዲያቀርቡ ዳዊት ለመደባቸው ካህናትና ሌዋውያን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ኀላፊነት ሰጣቸው። 19እንዲሁም በማንኛውም ነገር የረከሰ ሰው እንዳይገባ፣ በቤተ መቅደሱ ቅጥር በሮች ላይ ጠባቆች አቆመ። 20የመቶ አለቆቹን፣ መኳንንቱን፣ የሕዝቡን ገዦችና የአገሩን ሕዝብ ሁሉ ይዞ ንጉሡን ከላይ ከቤተ መቅደሱ ወደ ታች አመጣው። በላይኛውም መግቢያ በኩል ወደ ቤተ መንግሥቱ ገብተው ንጉሡን በመንግሥቱ ዙፋን ላይ አስቀመጡት። 21መላውም የአገሩ ሕዝብ ተደሰተ፤ ጎቶልያ ስለ ተገደለችም ከተማዪቱ ሰላም አግኝታ ነበር።
Copyright information for
AmhNASV