2 Samuel 22

የዳዊት የምስጋና መዝሙር

22፥1-51 ተጓ ምብ – መዝ 18፥1-50 1 እግዚአብሔር ከጠላቶቹ ሁሉና ከሳኦልም እጅ በታደገው ጊዜ፣ ዳዊት የዚህን መዝሙር ቃል ለእግዚአብሔር ዘመረ፤ 2እንዲህም አለ፤

እግዚአብሔር ዐለቴ ዐምባዬና ታዳጊዬ ነው፤
3አምላኬ፣ የምጠጋበት ዐለቴ፣
ጋሻዬና የድነቴ ቀንድ
ቀንድ የጥንካሬ ወይም የኀይል ምልክት ነው።
ነው።
እርሱም ጠንካራ ምሽጌ፣ መጠጊያና አዳኜ ነው፤
ከኀይለኞች ሰዎች ታድነኛለህ።
4ምስጋና የሚገባውን እግዚአብሔርን እጠራለሁ፤
ከጠላቶቼም እድናለሁ።

5“የሞት ማዕበል ከበበኝ፤
የጥፋትም ጐርፍ አሰጠመኝ።
6የሲኦል ገመድ ተጠመጠመብኝ፤
የሞትም ወጥመድ ተጋረጠብኝ።
7በጨነቀኝ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፤
ወደ አምላኬም ጮኽሁ።
እርሱም ከመቅደሱ ድምፄን ሰማ፤
ጩኸቴም ከጆሮው ደረሰ።
8ምድር ተንቀጠቀጠች፤ ተናወጠችም፤
የሰማያትም መሠረቶች
ዕብራይስጡ ከዚህ ጋር ይስማማል፤ ቩልጌትና ሱርስቱ ግን (እንዲሁም መዝ 18፥7 ይመ) ተራሮች ይላሉ።
ተናጉ፤
እርሱ ተቈጥቷልና ራዱ።
9ከአፍንጫው የቍጣ ጢስ ወጣ፤
ከአፉ የሚባላ እሳት ነደደ፤
ከውስጡም ፍሙ ጋለ።
10ሰማያትን ሰንጥቆ ወረደ፤
ከእግሩም በታች ጥቅጥቅ ያለ ደመና ነበረ።
11በኪሩቤል ላይ ተቀምጦ በረረ፤
በነፋስም ክንፍ መጠቀ።
አብዛኞቹ የዕብራይስጥ ቅጆች (እንዲሁም መዝ 18፥10 ይመ) ከዚህ ጋር ይስማማሉ፤ እጅግ ብዙ የሆኑ የዕብራይስጥ ቅጆች ግን፣ ተገለጠ ይላሉ።

12ጨለማው በዙሪያው እንዲከበው፣
ጥቅጥቅ ያለውም የሰማይ ዝናም ደመና እንዲሰውረው አደረገ።
13በእርሱ ፊት ካለው ብርሃን፣
የመብረቅ ብልጭታ ወጣ።
14 እግዚአብሔር ከሰማያት አንጐደጐደ፤
የልዑልም ድምፅ አስተጋባ።
15ፍላጻውን ሰድዶ ጠላቶቹን በተናቸው፤
መብረቆቹንም ልኮ አወካቸው።
16 ከእግዚአብሔር ተግሣጽ፣ ከአፍንጫው
ከሚወጣው፣ ከእስትንፋሱ ቍጣ የተነሣ፣
የባሕር ሸለቆዎች ታዩ፤ የምድር መሠረቶችም ተገለጡ።

17“ከላይ እጁን ዘርግቶ ያዘኝ፤
ከጥልቅ ውሆችም ውስጥ አወጣኝ።
18ከብርቱ ጠላቶቼ፣
ከማልቋቋማቸውም ባላጋሮቼ ታደገኝ።
19በመከራዬ ቀን መጡብኝ፤
እግዚአብሔር ግን ደገፈኝ።
20ሰፊ ወደ ሆነ ስፍራ አወጣኝ፤
በእኔ ደስ ስለ ተሰኘም አዳነኝ።

21እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ መለሰልኝ፤
እንደ እጄም ንጹሕነት ብድራትን ከፈለኝ፤
22 የእግዚአብሔርን መንገድ ጠብቄአለሁና፤
ከአምላኬም ዘወር ብዬ ክፉ ነገር አላደረግሁም።
23ሕጉ ሁሉ በፊቴ ነው፤
ከሥርዐቱም ዘወር አላልሁም።
24በፊቱ ያለ ነውር ነበርሁ፤
ራሴንም ከኀጢአት ጠብቄአለሁ።
25 እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ፣
በፊቱም እንዳለኝ ንጽሕና
ዕብራይስጡ ከዚህ ጋር ይስማማል፤ የሰብዓ ሊቃናትና የቩልጌት ትርጉሞች (እንዲሁም መዝ 18፥24 ይመ) ግን፣ እንደ እጄም ንጽሕና ይላሉ።
ብድራትን ከፈለኝ።

26“ለታማኝ ሰው አንተም ታማኝ መሆንህን፣
ለቅን ሰው አንተም ቅን መሆንህን ታሳያለህ።
27ለንጹሕ ሰው አንተም ንጹሕ መሆንህን፣
ለጠማማ ሰው ግን አንተም ጠማማ መሆንህን ታሳያለህ።
28አንተ የተጠቃውን ሕዝብ ታድናለህ፤
ዐይንህ ግን ያዋርዳቸው ዘንድ፣ ትዕቢተኞችን ይመለከታል።
29 እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ መብራቴ ነህ፤
እግዚአብሔርም ጨለማዬን ያበራል።
30በአንተ ርዳታ በጠላት ሰራዊት ላይ ወደ ፊት ገፍቼ እሄዳለሁ
ወይም በጋሬጣዎች ውስጥ እሮጣለሁ

በአምላኬም ኀይል ቅጥሩን እዘላለሁ።

31“የአምላክ መንገዱ ፍጹም ነው፤
የእግዚአብሔርም ቃል የነጠረ ነው፤
ለሚታመኑበትም ሁሉ ጋሻ ነው፤
32 ከእግዚአብሔር በቀር አምላክ ማን አለና፤
ከአምላካችንስ በቀር ዐለት ማን ነው?
33ኀይልን የሚያስታጥቀኝ
የሙት ባሕር ጥቅልል፣ አንዳንድ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕሞች፣ የቩልጌትና የሱርስት ቅጆች (እንዲሁም መዝ 18፥32 ይመ) ከዚህ ጋር ይስማማሉ፤ የማሶሬቱ ቅጅ ግን፣ ጠንካራ መሸሸጊያ የሚሆነኝ ይላል።

መንገዴንም የሚያቀና እርሱ አምላኬ ነው።
34እግሮቼን እንደ ብሆር እግሮች ያበረታል፤
በከፍታዎችም ላይ አጽንቶ ያቆመኛል።
35እጆቼን ለጦርነት ያሠለጥናል፤
ክንዶቼም የናስ ቀስት ይገትራሉ።
36የማዳንህን ጋሻ ሰጥተኸኛል፤
ድጋፍህ ታላቅ አድርጎኛል።
37ርምጃዬን አሰፋህ፤
እግሮቼም አልተሰነካከሉም።

38“ጠላቶቼን አሳደድሁ፤ አጠፋኋቸውም፤
እስኪደመሰሱም ድረስ ወደ ኋላ አልተመለስሁም።
39ፈጽሜ አጠፋኋቸው፤ ተመልሰውም መቆም አልቻሉም፤
ከእግሬም ሥር ወድቀዋል።
40ለጦርነት ኀይልን አስታጠቅኸኝ፣
ተቃዋሚዎቼንም ከእግሬ ሥር አንበረከክሃቸው።
41ጠላቶቼ ፊታቸውን አዙረው እንዲሸሹ አደረግሃቸው።
ባላንጣዎቼንም ደመሰስኋቸው።
42ለርዳታ ጮኹ፤ ያዳናቸው ግን አልነበረም፤ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱ ግን
አልመለሰላቸውም።
43በምድር ላይ እንዳለ ትቢያ አድቅቄ ፈጨኋቸው፤
በመንገድም ላይ እንዳለ ጭቃ ወቀጥኋቸው፤ ረገጥኋቸውም።

44“በሕዝቤ ከተቃጣብኝ አደጋ አዳንኸኝ፤
የመንግሥታትም ራስ አደረግኸኝ።
የማላውቀው ሕዝብ ተገዛልኝ፤
45ባዕዳን ሊለማመጡኝ መጡ፤
እንደ ሰሙኝም ወዲያውኑ ይታዘዙኛል።
46ባዕዳን ፈሩ፤
ከምሽጋቸውም እየተንቀጠቀጡ ወጡ
አንዳንድ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕሞችና የቩልጌቱ ቅጅ (እንዲሁም መዝ 18፥32 ይመ) ከዚህ ጋር ይስማማሉ፤ ማሶሬቱ ግን ራሳቸውን ጐዱ ይላል።


47እግዚአብሔር ሕያው ነው፤ ዐለቴ የተባረከ ይሁን፤
የድነቴ ዐለት አምላኬ ከፍ ከፍ ይበል።
48የሚበቀልልኝ አምላክ፣
መንግሥታትንም ከሥሬ የሚያስገዛልኝ እርሱ ነው፤
49እርሱ ከጠላቶቼ እጅ ነጻ ያወጣኛል።
አንተ ከጠላቶቼ በላይ ከፍ ከፍ አደረግኸኝ፤
ከጨካኝ ሰዎችም እጅ ታደግኸኝ።
50ስለዚህ እግዚአብሔር ሆይ፤
በመንግሥታት መካከል አመሰግንሃለሁ፤ ለስምህም ምስጋና እዘምራለሁ።

51“ለንጉሡ ታላቅ ድል ይሰጠዋል፤
ለቀባው ለዳዊትና ለዘሩ፣
ለዘላለም የማይለወጥ ፍቅሩን ያሳየዋል።”
Copyright information for AmhNASV