2 Samuel 23
የዳዊት የመጨረሻ ቃል
1የዳዊት የመጨረሻ ቃሉ ይህ ነው፤“በያዕቆብ አምላክ የተቀባው፣
ልዑል ከፍ ከፍ ያደረገው ሰው፣
የእስራኤል ተወዳጁ ዘማሪ፣
የእሴይ ልጅ የዳዊት የትንቢት ቃል ይህ ነው፤
2“የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ተናገረ፤
ቃሉ በአንደበቴ ላይ ነበረ።
3የእስራኤል አምላክ ተናገረ፤
የእስራኤልም ዐለት እንዲህ አለኝ፤
‘ሰዎችን በጽድቅ የሚገዛ፣
በፈሪሀ እግዚአብሔርም የሚያስተዳድር፣
4እርሱ፣ ደመና በሌለበት፣ በማለዳ ፀሓይ በምትወጣበት ጊዜ፣
እንዳለው ብርሃን ነው፤
በምድር ላይ ሣርን እንደሚያበቅለው፣
ከዝናብም በኋላ እንዳለው የብርሃን ጸዳል ነው።’
5“የእኔስ ቤት በእግዚአብሔር ዘንድ ትክክል አይደለምን?
ሁሉንም ነገር አዘጋጅቶና ጠብቆ፣
ከእኔ ጋር ዘላለማዊ ኪዳን ያደረገ አይደለምን?
ድነቴን ከፍጻሜ የሚያደርሰው፣
መሻቴን ሁሉ የሚሰጠኝ እርሱ አይደለምን?
6ነገር ግን ክፉ ሰዎች ሁሉ፣
በእጅ እንደማይሰበሰብ እንደ እሾኽ ይጣላሉ።
7እሾኽ የሚነካ ሁሉ፣
የብረት መሣሪያ ወይም የጦር ዘንግ ይይዛል፤
ባሉበትም ቦታ ፈጽመው በእሳት ይቃጠላሉ።”
የኀያላኑ የዳዊት ሰዎች ጀብዱ
23፥8-39 ተጓ ምብ – 1ዜና 11፥10-41 8የዳዊት ኀያላን ሰዎች ስም የሚከተለው ነው፤የታሕክሞን ▼ ሰው ዮሴብ በሴትቤት ▼ የሦስቱ አለቆች አለቃ ሲሆን፣ እርሱም ጦሩን ሰብቆ በአንድ ውጊያ ላይ ስምንት መቶ ሰው የገደለ ነው። ▼
9ከእርሱ ቀጥሎ የአሆሃዊው የዱዲ ልጅ ኤልዔዘር ነበረ፤ እርሱም ለጦርነት አንድ ላይ ተሰብስበው ▼ የነበሩትን ፍልስጥኤማውያንን በተገዳደሩ ጊዜ፣ ከዳዊት ጋር ከነበሩት ከሦስቱ ኀያላን ሰዎች አንዱ ነበር። ከዚያም የእስራኤል ሰዎች ሸሹ። 10እርሱ ግን የቆመበትን ስፍራ አልለቀቀም፤ እጁ እስኪዝልና ከሰይፉ ጋር እስኪጣበቅ ድረስ ፍልስጥኤማውያንን ወጋ፤ በዚያችም ዕለት እግዚአብሔር ታላቅ ድልን ሰጠ። የሸሸውም ሰራዊት ወደ ኤልዔዘር የተመለሰው የተገደሉትን ሰዎች ለመግፈፍ ብቻ ነበር።
11ከእርሱም ቀጥሎ የአሮዳዊው የአጌ ልጅ ሣማ ነበር፤ ፍልስጥኤማውያንም ሌሒ በተባለ ስፍራ ምስር በሞላበት አንድ ዕርሻ ላይ በአንድነት ተሰብስበው ሳሉ፣ የእስራኤል ሰራዊት ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፤ 12ሣማ ግን የቆመበትን ስፍራ አልለቀቀም፤ ጦርነቱንም ተቋቁሞ ፍልስጥኤማውያንን ገደለ፤ በዚያችም ዕለት እግዚአብሔር ታላቅ ድል ሰጠ።
13በመከር ወራት፣ የፍልስጥኤም ሰራዊት በራፋይም ሸለቆ ሰፍሮ ሳለ፣ ከሠላሳዎቹ አለቆች ሦስቱ ዳዊት ወዳለበት ወደ ዓዶላም ዋሻ መጡ። 14በዚያም ጊዜ ዳዊት በምሽግ ውስጥ ነበረ፤ የፍልስጥኤማውያንም ሰራዊት በቤተ ልሔም ነበረ፤ 15ዳዊትም በናፍቆት፣ “በቤተ ልሔም በር አጠገብ ካለችው ጕድጓድ ውሃ ማን ባመጣልኝ!” አለ። 16ስለዚህ ሦስቱ ኀያላን በፍልስጥኤማውያን ሰራዊት መካከል ሰንጥቀው በማለፍ፣ በቤተ ልሔም በር አጠገብ ካለችው ጕድጓድ ውሃ ቀድተው ለዳዊት አመጡለት። እርሱ ግን አልጠጣውም፤ ይልቁን በእግዚአብሔር ፊት መሥዋዕት አድርጎ አፈሰሰው፤ 17“እርሱም፣ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንዲህ ያለውን ነገር ላደርግ? ይህስ ከእኔ ይራቅ! ይህ በነፍሳቸው ቈርጠው የሄዱ ሰዎች ደም አይደለምን?” አለ፤ ዳዊትም ሊጠጣው አልፈለገም። እንግዲህ ሦስቱ ኀያላን ሰዎች ያደረጉት ጀብዱ እንዲህ ነበር።
18የጽሩያ ልጅ የኢዮአብ ወንድም አቢሳ የሦስቱ ▼ ኀያላን አለቃ ነበረ። በሦስት መቶ ሰዎች ላይ ጦሩን ሰብቆ የገደላቸውና እንደ ሦስቱ ኀያላን ሁሉ እርሱም ዝናን ያተረፈ ሰው ነበረ። 19አቢሳ ከሦስቱ ይልቅ እጅግ የከበረ አልነበረምን? ከእነርሱ እንደ አንዱ ባይሆንም አለቃቸው ነበረ።
20የቀብጽኤል አገር ሰው የሆነው የዮዳሄ ልጅ በናያስ ታላቅ ጀብዱ የሠራ ሌላው ጐበዝ ተዋጊ ነበረ፤ እርሱም ሁለት በጣም የታወቁ የሞዓብ ሰዎችን ገደለ፤ እንዲሁም በረዶ በጣለበት ዕለት በጕድጓድ ውስጥ ገብቶ አንበሳ ገድሏል፤ 21ደግሞም አንድ ግዙፍ ግብፃዊ ገድሏል፤ ግብፃዊው በእጁ ጦር የያዘ ቢሆንም፣ በናያስ ግን ሊገጥመው በትር ይዞ ወደ እርሱ ሄደ፤ ከግብፃዊውም እጅ ጦሩን በመንጠቅ በገዛ ጦሩ ገደለው።
22የዮዳሄ ልጅ የበናያስ ጀግንነት እንደዚህ ያለ ነበረ፤ እርሱም እንደ ሦስቱ ኀያላን ሁሉ ዝናን ያተረፈ ሲሆን፣ 23ከሠላሳዎቹ ሁሉ በላይ የከበረ ሰው ነበረ፤ ነገር ግን ከሦስቱ እንደ አንዱ አልነበረም። ዳዊትም የክብር ዘበኞቹ አለቃ አድርጎ ሾመው።
24ከሠላሳዎቹ መካከል የሚከተሉት ይገኙባቸዋል፤
የኢዮአብ ወንድም አሣሄል፣
የቤተ ልሔሙ ሰው የዱዲ ልጅ ኤልያናን፣
25አሮዳዊው ሣማ፣
አሮዳዊው ኤሊቃ፣
26ፈሊጣዊው ሴሌስ፣
የቴቁሐዊው የዒስካ ልጅ ዒራስ፣
27ዓናቶታዊው አቢዔዜር፤
ኩሳታዊው ምቡናይ ▼፣
28አሆሃዊው ጸልሞን፣
ነጦፋዊው ማህራይ፣
29የነጦፋዊው የበዓና ልጅ ሔሌብ ▼፣
ከብንያም ወገን የጊብዓ ሰው የሆነው የሪባይ ልጅ ኢታይ፣
30ጲርዓቶናዊው በናያስ፣
የገዓስ ሸለቆ ሰው ሂዳይ ▼፣
31ዐረባዊው አቢዓልቦን፣
በርሑማዊው ዓዝሞት፣
32ሸዓልቦናዊው ኤሊያሕባ፣
የአሳን ልጆች፤ ዮናታን የተባለው፣
33የአሮዳዊው የሣማ ልጅ ▼፣
የአሮዳዊው የሻራር ▼ ልጅ አሒአም፤
34የማዕካታዊው የአሐሰባይ ልጅ ኤሌፋላት፣
የጊሎናዊው የአኪጦፌል ልጅ ኤሊአም፣
35ቀርሜሎሳዊው ሐጽሮ፤
አርባዊው ፈዓራይ፣
36የሱባ ሰው የሆነው የናታን ልጅ ይግዓል፣
37አሞናዊው ጻሌቅ፣
የጽሩያ ልጅ የኢዮአብ ጦር መሣሪያ ያዥ የነበረው ብኤሮታዊው ነሃራይ፣
38ይትራዊው ዒራስ፣
ይትራዊው ጋሬብ፣
39እንዲሁም ኬጢያዊው ኦርዮ።
በጠቅላላው ሠላሳ ሰባት ነበሩ።
Copyright information for
AmhNASV