‏ Deuteronomy 10

በድጋሚ የተሰጡ የመጀመሪያዎቹ ዐይነት ጽላቶች

1በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ አለኝ፤ “እንደ መጀመሪያዎቹ ያሉ ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ቀርጸህ ወደ እኔ ወደ ተራራው ላይ ውጣ፤ ታቦትም ከዕንጨት ሥራ። 2እኔም አንተ በሰበርሃቸው በፊተኞቹ ጽላቶች ላይ የነበሩትን ቃላት በእነዚህኞቹ ጽላቶች ላይ እጽፋቸዋለሁ፤ አንተም በታቦቱ ውስጥ ታኖራቸዋለህ።”

3ስለዚህ ከግራር ዕንጨት ታቦት ሠራሁ፤ እንደ ፊተኞቹ ያሉ ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ቀረጽሁ፤ ሁለቱንም ጽላቶች በእጆቼ ይዤ ወደ ተራራው ወጣሁ። 4እግዚአብሔር (ያህዌ) በስብሰባው ቀን፣ በእሳት ውስጥ ሆኖ ለእናንተ የተናገራቸውንና ቀድሞ ጽፏቸው የነበሩትን ዐሥሩን ትእዛዞች በእነዚህ ጽላቶች ላይ ጻፋቸው። እግዚአብሔርም (ያህዌ) እነርሱን ለእኔ ሰጠኝ። 5ከዚያም ከተራራው ተመልሼ ወረድሁ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ባዘዘኝ መሠረት በሠራሁት ታቦትም ውስጥ፣ ጽላቶቹን አስቀመጥኋቸው፤ አሁንም እዚያ ናቸው።

6እስራኤላውያን ከብኤሮት ብኔያዕቃን፣ የያዕቃን ልጆች ከቈፈሯቸው የውሃ ጕድጓዶች ተነሥተው ወደ ሞሴራ ተጓዙ፤ አሮንም በዚያ ቦታ ሞቶ ተቀበረ፤ ልጁ አልዓዛር በእርሱ ምትክ ካህን ሆነ። 7ከዚያም ተነሥተው ጕድጎዳ ወደ ተባለ ስፍራ፣ ቀጥሎም የውሃ ፈሳሾች ወዳሉባት ዮጥባታ ወደምትባል ምድር ተጓዙ። 8በዚያን ጊዜ፣ ዛሬም እንደሚያደርገው ያገለግል ዘንድ፣ በእግዚአብሔርም (ያህዌ) ፊት እንዲቆምና በስሙ እንዲባርክ የእግዚአብሔርንም (ያህዌ) የኪዳኑን ታቦት እንዲሸከም እግዚአብሔር (ያህዌ) የሌዊን ነገድ ለየ። 9ሌዋዊ በወንድሞቹ መካከል ድርሻም ሆነ ርስት የሌለው ከዚህ የተነሣ ነው፤ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በነገረው መሠረት ርስቱ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነው።

10እኔም በመጀመሪያው ጊዜ እንዳደረግሁት፣ በተራራው ላይ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ቈየሁ፤ በዚህ ጊዜም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ገና ሰማኝ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) አንተን ሊያጠፋ አልፈቀደም። 11ስለዚህም እግዚአብሔር (ያህዌ)፣ “ሂድ፤ ለአባቶቻቸው ለመስጠት ወደ ማልሁላቸው ምድር ገብተው እንዲወርሱ ሕዝቡን ምራ” አለኝ።

እግዚአብሔርን (ያህዌ) ፍራ

12አሁንም እስራኤል ሆይ፤ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) እንድትፈራው፣ በመንገዶቹ ሁሉ እንድትሄድ፣ እንድትወድደው፣ በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ እንድታገለግለው፣ 13መልካም እንዲሆንልህና ዛሬ እኔ የምሰጥህን ትእዛዞችና ሥርዐቶች እንድትጠብቅ አይደለምን?

14ሰማያት፣ ሰማየ ሰማያት፣ ምድርና በእርሷም ያለው ሁሉ የአምላክህ የእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ነው። 15ነገር ግን እግዚአብሔር (ያህዌ) አባቶችህን ስላፈቀረ፣ ወደዳቸው፤ ዛሬም እንደ ሆነው የእነርሱ ዘር የሆናችሁትን እናንተን ከአሕዛብ ሁሉ ለይቶ መረጣችሁ። 16ስለዚህ የልባችሁን ሸለፈት ግረዙት፤ ከእንግዲህም ወዲያ ዐንገተ ደንዳና አትሁኑ። 17አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የአማልክት አምላክ (ኤሎሂም)፣ የጌቶች ጌታ (አዶናይ) ታላቅ አምላክ (ኤሎሂም)፣ ኀያልና የሚያስፈራ፣ አድልዎ የማያደርግ፣ መማለጃም የማይቀበል ነውና። 18እርሱ አባት ለሌላቸውና ለመበለቶች ይፈርዳል፤ መጻተኛውንም ምግብና ልብስ በመስጠት ይወድዳል። 19ስለዚህ እናንተም በግብፅ ምድር መጻተኞች ነበራችሁና መጻተኛን ውደዱ። 20አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ፍራ፤ አምልከውም፤ ከእርሱም ጋር ተጣበቅ፤ በስሙም ማል። 21እርሱ ውዳሴህ ነው፤ በገዛ ዐይኖችህ ያየሃቸውን፣ እነዚያን ታላላቅና አስፈሪ ነገሮች ያደረገልህ አምላክህ (ኤሎሂም) ነው። 22አባቶችህ ወደ ግብፅ ሲወርዱ ሰባ ነበሩ፤ አሁን ግን አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እንደ ሰማይ ከዋክብት አብዝቶሃል።

Copyright information for AmhNASV