‏ Exodus 31

ባስልኤልና ኤልያብ

31፥2-6 ተጓ ምብ – ዘፀ 35፥30-35 1ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2“እነሆ፤ ከይሁዳ ነገድ የሆር የልጅ ልጅ የሆነውን የኡሪን ልጅ ባስልኤልን መርጬዋለሁ። 3በሁሉም ዐይነት የእጅ ጥበብ ሥራ፣ ብልኀት፣ ችሎታና ዕውቀት እንዲኖረው የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም) መንፈስ ሞልቼዋለሁ። 4ይኸውም በወርቅ፣ በብርና በናስ ለሚሠሩት ሥራዎች በጥበብ የተሠሩ ጌጦችን እንዲያበጅ፣ 5ድንጋዮችን እንዲቈፍርና እንዲጠርብ ከዕንጨትም ጥርብ እንዲያወጣ፣ ሁሉንም ዐይነት የእጅ ጥበብ ሥራዎችን እንዲያከናውን ነው። 6በተጨማሪም ከዳን ነገድ የሆነውን የአሂሳሚክን ልጅ ኤልያብን እንዲረዳው መርጬዋለሁ፤ እንዲሁም ያዘዝሁህን ሁሉ ያደርጉ ዘንድ ለእጅ ጥበብ ዐዋቂዎች ሁሉ ብልኀትን ሰጥቻቸዋለሁ፤

7“ይኸውም የመገናኛውን ድንኳን፣
የምስክሩን ታቦት በላዩ ላይ ካለው ከስርየት መክደኛው ጋር፣
ሌሎች የድንኳኑን መገልገያ ዕቃዎች ሁሉ፣
8ጠረጴዛውን ከነዕቃዎቹ፣
ከንጹሕ ወርቅ የተሠራውን የወርቅ መቅረዝ ከነዕቃዎቹ፣
የዕጣኑን መሠዊያ፣
9የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያውን ከነዕቃዎቹ፣
ሰኑን፣ ከነማስቀመጫው፣
10ከፈትል የተሠሩ ልብሶችን ይኸውም የካህኑን የአሮንን የተቀደሱ ልብሶችንና ካህናት ሆነው ሲያገለግሉ የሚለብሷቸውን የወንድ ልጆቹ ልብሶች፣
11እንዲሁም የመቅደሱ የሆነውን ቅብዐ ዘይትና ጣፋጭ ሽታ ያለውን ዕጣን እንዲሠሩ ነው።

“ልክ እኔ እንዳዘዝሁህ ያብጇቸው።”

ሰንበት

12ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ 13“ለእስራኤላውያን ንገራቸው፤ ‘ሰንበቴን ማክበር አለባችሁ፤ ይህም በእኔና በእናንተ መካከል በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ምልክት ይሆናል፤ ይኸውም የምቀድሳችሁ
ወይም፣ ቅዱስ አድርጌ የምለያችሁ
እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ሆንሁ እንድታውቁ ነው።

14“ ‘ለእናንተ ቅዱስ ነውና ሰንበትን አክብሩ፤ ማንም ቢሽረው በሞት ይቀጣል፤ በዚያ ቀን ማንም የሚሠራ ቢኖር ከወገኑ ተነጥሎ ይለይ። 15ስድስት ቀን ሥራ ይሠራል፤ ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተቀደሰ የዕረፍት ሰንበት ነው፤ በሰንበት ቀን ማንም ቢሠራ በሞት መቀጣት አለበት። 16እስራኤላውያን በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ሰንበትን በመጠበቅ የዘላለም ኪዳን አድርገው ማክበር አለባቸው፤ 17በእኔና በእስራኤላውያን መካከል ለዘላለም ምልክት ይሆናል፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሰማይንና ምድርን በስድስት ቀን ሠርቶ፣ በሰባተኛው ቀን ከሥራ ታቅቦ ዐርፏልና።’ ”

18 እግዚአብሔር (ያህዌ) በሲና ተራራ ላይ ለሙሴ መናገሩን ከፈጸመ በኋላ፣ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ጣት የተጻፈባቸውን የድንጋይ ጽላቶች፣ ሁለቱን የምስክር ጽላቶች ለእርሱ ሰጠው።

Copyright information for AmhNASV