‏ Exodus 35

የሰንበት ሥርዐቶች

1ሙሴ የእስራኤልን ማኅበረ ሰብ ሁሉ ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) እንድትፈጽሟቸው ያዘዛችሁ ነገሮች እነዚህ ናቸው፤ 2ስድስት ቀን ሥራ ይሠራል፤ ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሰንበት ዕረፍት፣ የተቀደሰ ቀን ይሆንላችኋል፤ በዕለቱ ማናቸውንም ዐይነት ሥራ የሚሠራ ቢኖር ሞት ይገባዋል። 3በሰንበት ቀን በማናቸውም መኖሪያዎቻችሁ ውስጥ እሳት አታንድዱ።”

ለመገናኛው ድንኳን ዕቃዎች

35፥4-9 ተጓ ምብ – ዘፀ 25፥1-7 35፥10-19 ተጓ ምብ – ዘፀ 39፥32-41 4ሙሴ ለእስራኤላውያን ማኅበረ ሰብ ሁሉ እንዲህ አላቸው፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዘው ይህ ነው፤ 5ካላችሁ ንብረት ሁሉ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕት አቅርቡ፤ ፈቃደኛ የሆነ ማንም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የወርቅ፣ የብር፣ የናስ መባ ያምጣ። 6ሰማያዊ፣ ሐምራዊና ቀይ ማግ፤ ቀጭን ሐር፣ የፍየል ጠጕር፣ 7ቀይ የተነከረ የአውራ በግ ቈዳ፣ እንዲሁም አቆስጣ ቈዳ
በዚህና በቍጥር 23 ላይ አንዳንድ ቅጆች፣ የለፋ የአቆስጣ ቈዳ ይላሉ።
፣ የግራር ዕንጨት፤
8ለመብራት የወይራ ዘይት፣ ለቅብዐ ዘይቱና ለጣፋጭ ሽታ ዕጣን ቅመም፤ 9በኤፉዱና በደረት ኪሱ ላይ የሚሆኑ መረግዶችና ሌሎች ዕንቍዎችን መባ አድርጎ ያምጣ።

10“በመካከላችሁ ጥበበኞች የሆኑ ሁሉ መጥተው እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዘውን ሁሉ ይሥሩ፤ 11የመገናኛውን ድንኳን ከነድንኳኑና ከነመደረቢያው፣ ማያያዣዎችን፣ ክፈፎችን፣ አግዳሚዎችን፣ ቋሚዎችንና መሠረቶችን፤ 12ታቦቱን ከነመሎጊያዎቹ፣ የስርየት መክደኛውንና የሚሸፍነውን መጋረጃ፤ 13ጠረጴዛውን ከነመሎጊያዎቹ፣ ዕቃዎቹን ሁሉና የሀልዎቱን ኅብስት፤ 14ለመብራት የሆነውን መቅረዝ ከነዕቃዎቹ፣ ቀንዲሎችንና ለመብራት የሚሆነውን ዘይት፤ 15የዕጣን መሠዊያውን ከነመሎጊያዎቹ፣ ቅብዐ ዘይቱንና ጣፋጭ ሽታ ያለውን ዕጣን፤ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ የሚሆነውን የመግቢያ መጋረጃ፤ 16የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያውን ከናስ መጫሪያው፣ መሎጊያዎቹንና ዕቃዎቹን ሁሉ፣ የናስ ሰኑን ከነማስቀመጫው፣ 17የአደባባዩን መጋረጃዎች ከነምሰሶዎቻቸውና ከነመሠረቶቹ፣ ያደባባዩን መግቢያ መጋረጃ፤ 18ለመገናኛው ድንኳንና ለአደባባዩ የሚሆኑ የድንኳን ካስማዎችና ገመዶቻቸው፤ 19በመቅደሱ ውስጥ ለማገልገል የሚለበሱ የፈትል ልብሶችን ይኸውም የካህኑ የአሮንን የተቀደሱ ልብሶችንና ካህናት ሆነው ሲያገለግሉ የሚለብሷቸውን የወንዶች ልጆቹን ልብሶች ይሥሩ።”

20ከዚያም የእስራኤል ማኅበረ ሰብ ሁሉ ከሙሴ ፊት ወጡ፤ 21ፈቃደኛ የነበረና ልቡን ያነሣሣው ሁሉ በመምጣት ለመገናኛው ድንኳን ሥራ፣ ለአገልግሎቱ ሁሉና ለተቀደሱ ልብሶች የሚሆን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መባ አመጡ። 22ፈቃደኛ የነበሩ ሁሉ፣ ወንዶችም ሴቶችም መጥተው ከሁሉም ዐይነት የወርቅ ጌጦች አመጡ፤ የአፍንጫ ጌጦችን፣ ሎቲዎችን፣ ቀለበቶችን፣ ድሪዎችንና ጌጣጌጦችን ሁሉ አመጡ፤ ሁሉም ወርቃቸውን እንደሚወዘወዝ መሥዋዕት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቀረቡ። 23ሰማያዊ፣ ሐምራዊ ወይም ቀይ ማግ ወይም ቀጭን ሐር ወይም የፍየል ጠጕር፣ ቀይ የተነከረ የአውራ በግ ቈዳ ወይም የአቆስጣ ቈዳ አመጡ። 24የብር ወይም የናስ መባ ማቅረብ የቻሉ ሁሉ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መባ አድርገው አመጡ፤ የግራር ዕንጨት ያለው ሁሉ አስፈላጊ በሆነው ሥራ እንዲውል አመጣው። 25ጥበበኞች የሆኑ ሴቶች ሁሉ በእጃቸው ፈተሉ፤ የፈተሉትንም ሰማያዊ ሐምራዊ ወይም ቀይ ማግ ወይም ቀጭን በፍታ አመጡ። 26ፈቃደኛ የነበሩና ጥበቡ ያላቸው ሴቶች ሁሉ የፍየል ጠጕር ፈተሉ። 27መሪዎቹም ኤፉድና በደረት ኪሱ ላይ እንዲሆን የከበሩ ድንጋዮችንና ሌሎች ዕንቍዎች አመጡ። 28እንዲሁም ለመብራቱ፣ ለቅብዐ ዘይቱና ለጣፋጭ ሽታ ዕጣን የሚሆኑ ቅመሞችንና የወይራ ዘይትን አመጡ። 29ፈቃደኛ የሆኑ እስራኤላውያን ወንዶችና ሴቶች ሁሉ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) በሙሴ በኩል እንዲያከናውኑት ላዘዛቸው ሥራ ሁሉ የበጎ ፈቃድ ስጦታዎችን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አመጡ።

ባስልኤልና ኤልያብ

35፥30-35 ተጓ ምብ – ዘፀ 31፥2-6 30ከዚያም ሙሴ እስራኤላውያንን አላቸው፤ “እነሆ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ከይሁዳ ነገድ የሆነውን የሆር ልጅ፣ የኡሪን ልጅ ባስልኤልን መርጧል። 31በጥበብ፣ በችሎታና በዕውቀት፣ በማናቸውም ዐይነት ሙያ የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም) መንፈስ ሞልቶበታል፤ 32ይኸውም በወርቅ፣ በብርና በናስ የጥበብ ሥራ እንዲሠራ ነው፤ 33ድንጋዮችን እንዲጠርብና እንዲያወጣ፣ የዕንጨት ሥራ እንዲሠራና ማንኛውንም ዐይነት የጥበብ ሙያ እንዲያከናውን ነው። 34እንዲሁም ለእርሱና ከዳን ነገድ ለሆነው ለአሂሳሚክ ልጅ ለኤልያብ፣ ለሁለቱም ሌሎችን የማስተማር ችሎታ ሰጣቸው። 35የጥበብ ባለሙያዎች፣ ዕቅድ አውጭዎች፣ በሰማያዊ በሐምራዊና በቀይ ማግ፣ በቀጭን ሐር ጥልፍ ጠላፊዎችና ፈታዮች፤ ሁሉም ዋና የጥበብ ባለሙያዎችና ዕቅድ አውጭዎች በመሆን ማንኛውንም ዐይነት ሥራ ያከናውኑ ዘንድ በጥበብ ሞልቷቸዋል።

Copyright information for AmhNASV