Ezekiel 21

የቅጣት በትር የሆነችው ባቢሎን

1 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 2“የሰው ልጅ ሆይ፤ ፊትህን ወደ ኢየሩሳሌም አዙር፤ በመቅደሱ ላይ ቃል ተናገር፤ በእስራኤል ምድር ላይ ትንቢት ተንብይ፤ 3እንዲህም በል፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ እኔ በአንቺ ላይ ተነሥቻለሁ፤ ሰይፌን ከሰገባው እመዝዛለሁ፤ ጻድቁንም፣ ክፉውንም ከአንተ ዘንድ አስወግዳለሁ። 4ጻድቁንም ክፉውንም ስለማስወግድ ሰይፌ ከደቡብ ጀምሮ እስከ ሰሜን ባለው ሕዝብ ሁሉ ላይ ከሰገባው ይመዘዛል። 5ሰይፌን ከሰገባው የመዘዝሁት እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ሕዝቡ ሁሉ ያውቃል፤ እርሱም ወደ ሰገባው አይመለስም።’

6“ስለዚህ የሰው ልጅ ሆይ፤ አቃስት፤ በተሰበረ ልብና በመረረ ሐዘን አቃስት፤ 7እነርሱም፣ ‘ለምን ታቃስታለህ?’ ቢሉህ፣ ‘ስለሚመጣው ክፉ ወሬ ነው፤ ልብ ሁሉ ይቀልጣል፤ እጅም ሁሉ ይዝላል፤ ነፍስ ሁሉ ይደክማል፤ ጕልበትም ሁሉ ውሃ ይሆናል’ በላቸው። እነሆ ይመጣል፤ ይፈጸማልም፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።”

8 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 9“የሰው ልጅ ሆይ፤ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በል፤ ‘ጌታ እንዲህ ይላል፤

“ ‘ሰይፍ! ሰይፍ!
የተሳለ የተወለወለም፤
10የተሳለው ሊገድል፣
የተወለወለውም እንደ መብረቅ ሊብረቀረቅ ነው!
“ ‘ታዲያ፣ እንዴት ደስ ሊለን ይችላል? ሰይፉ የልጄን በትረ መንግሥት እንደ ማንኛውም በትር ንቋል።

11“ ‘በእጁ እንዲያዝ፣
ሰይፉ ሊወለወል ተሰጥቷል፤
ገዳዩ በእጁ እንዲጨብጠው፣
ተስሏል፤ ተወልውሏል።
12የሰው ልጅ ሆይ፤ ይህ በሕዝቤ ላይ፣
በእስራኤልም መሳፍንት ሁሉ ላይ መጥቷልና፤
ጩኸት፣ ዋይታም አሰማ።
እነርሱ ከሕዝቤ ጋር በአንድ ላይ፣
ለሰይፍ ተጥለዋል፤
ስለዚህ ደረትህን ምታ።
13“ ‘ፈተና በርግጥ ይመጣል፤ ሰይፉ የናቀው በትረ መንግሥት ዘላቂነት ባይኖረውስ? ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’

14“እንግዲህ፣ የሰው ልጅ ሆይ፤ ትንቢት ተናገር፤
በእጅህም አጨብጭብ፤
ሰይፉ ሁለት ጊዜ፣
ሦስት ጊዜም ይምታ፤
በእጅጉ የሚገድል፣
ለግድያ የሚሆን፣
በየአቅጣጫውም የሚከባቸው ሰይፍ ነው።
15ልብ ሁሉ ይቀልጥ ዘንድ፣
የሚወድቁትም እንዲበዙ፣
በበሮቻቸው ሁሉ፣
የግድያውን ሰይፍ
ከሰብዐ ሊቃናት ጋር ተመሳሳይ ሲሆን በዕብራይስጡ ግን የዚህ ቃል ትርጕም አይታወቅም።
አኑሬአለሁ።
ወዮ! እንዲያብረቀርቅ ተወልውሏል፤
ለመግደልም ተመዝዟል።
16ሰይፍ ሆይ፤ በስለትህ አቅጣጫ ሁሉ፣
ወደ ቀኝም፣
ወደ ግራም ቍረጥ።
17እኔም በእጄ አጨበጭባለሁ፤
ቍጣዬም ይበርዳል፤
እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ።”
18 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 19“የሰው ልጅ ሆይ፤ የባቢሎን ንጉሥ ሰይፍ የሚመጣባቸውን የሁለት መንገዶች ካርታ ንደፍ፤ መንገዶቹም ከአንድ አገር የሚነሡ ናቸው፤ መንገዱ ወደ ከተማው በሚገነጠልበት ቦታ ላይ ምልክት አቁም። 20በአሞናውያን ከተማ በረባት ላይ ለሚመጣው ሰይፍ አንደኛውን መንገድ ምልክት አድርግ፤ በይሁዳና በተመሸገችው ከተማ በኢየሩሳሌም ላይ ለሚመጣውም ሰይፍ ሁለተኛውን መንገድ ምልክት አድርግ። 21የባቢሎን ንጉሥ በጥንቈላ ምሪት ለማግኘት በመንታ መንገድ ላይ በሁለቱ ጐዳናዎች መጋጠሚያ ላይ ይቆማል፤ ቀስቶቹን በመወዝወዝ ዕጣ ይጥላል፤ አማልክቱን ያማክራል፤ ጕበትንም ይመረምራል። 22የቅጥር መደርመሻ አምጥቶ እንዲያቆም፣ ለመግደል ትእዛዝ እንዲሰጥ፣ ፉከራ እንዲያሰማ፣ ቅጥር መደርመሻውን በከተሞች በር ላይ እንዲያደርግ፣ የዐፈር ድልድል እንዲያበጅና ምሽግ እንዲሠራ የኢየሩሳሌም ዕጣ በቀኝ እጁ ወጣ። 23ይህም ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን ለገቡት የተሳሳተ ምሪት ይመስላል፤ እርሱ ግን በደላቸውን ያሳስባቸዋል፤ ማርኮም ይዟቸው ይሄዳል።

24“ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እናንተ በምታደርጉት ሁሉ ኀጢአታችሁን በመግለጽ፣ በግልጽም በማመፅ በደላችሁን ስላሳሰባችሁ፣ እንዲህም ስላደረጋችሁ በምርኮ ትወሰዳላችሁ።

25“ ‘አንተ የግፍ ጽዋህ የሞላ፣ የምትቀጣበት ቀን የደረሰ፣ ርኩስና ክፉ የእስራኤል መስፍን ሆይ፤ 26ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ጥምጥምህን አውልቅ፤ ዘውድህን ጣል፤ እንደ ከዚህ በፊቱ አይሆንም፤ ዝቅ ያለው ከፍ ይላል፤ ከፍ ያለውም ዝቅ ይላል። 27ባድማ! ባድማ! ባድማ አደርጋታለሁ፤ የሚገባው ባለ መብት እስከሚመጣ ድረስ እንደ ቀድሞው አትሆንም፤ ለእርሱም ደግሞ እሰጣታለሁ።” ’

28“አንተ የሰው ልጅ ሆይ! እንዲህ ብለህ ተናገር፤ ‘ስለ አሞናውያንና ስለ ስድባቸው ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

“ ‘ሰይፍ! ሰይፍ!
ሊገድል የተመዘዘ፣
ሊያጠፋ የተጠረገ፣
እንደ መብረቅ ሊያብረቀርቅ የተወለወለ፤
29የታለመልህ የሐሰት ራእይ፣
የተነገረልህ የውሸት ሟርት ቢኖርም፣
የግፍ ጽዋቸው በሞላ፣
ቀናቸው በደረሰ፣
መታረድ በሚገባቸው ክፉዎች፣
ዐንገት ላይ ይሆናል።

30“ ‘ሰይፉን ወደ ሰገባው መልሰው፤
በተፈጠርህበት ምድር፣
በተወለድህበትም አገር፣
በዚያ እፈርድብሃለሁ።
31መዓቴን በላይህ አፈስሳለሁ፤
የቍጣዬንም እሳት አነድድብሃለሁ፣
በጥፋት ለተካኑ፣
ለጨካኞች ሰዎች አሳልፌ እሰጥሃለሁ።
32ለእሳት ማገዶ ትሆናለህ፣
ደምህ በምድርህ ይፈስሳል፣
ከእንግዲህ መታሰቢያ አይኖርህም፤
እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁና።’ ”
Copyright information for AmhNASV