Ezekiel 7

ፍጻሜው ደረሰ

1 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 2“አንተ የሰው ልጅ ሆይ፤ ጌታ እግዚአብሔር ለእስራኤል ምድር እንዲህ ይላል፤

“ ‘ፍጻሜ! በአራቱም የምድሪቱ ማእዘን
ፍጻሜ መጥቷል!
3አሁንም መጨረሻሽ ደርሷል፤
ቍጣዬን በአንቺ ላይ አፈስሳለሁ፤
እንደ አካሄድሽ እፈርድብሻለሁ፤
ስለ ጸያፍ ተግባርሽ ሁሉ፣
ተገቢውን ቅጣት እከፍልሻለሁ።
4በርኅራኄ ዐይን አልመለከትሽም፤
ምሕረትም አላደርግልሽም፤
ስለ አካሄድሽና በመካከልሽ ስላለው ጸያፍ ተግባር፣
ተገቢውን ቅጣት እከፍልሻለሁ፤
በዚያ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።’

5“ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

“ ‘መዓት! ተሰምቶ የማይታወቅ መዓት
አብዛኛዎቹ የዕብራይስጥ የጥንት ቅጆች እንዲሁ ናቸው፤ አንዳንድ የዕብራይስጥና የሱርስት የጥንት ቅጆች ግን በጥፋት ላይ ጥፋት ይላሉ
ይመጣል።
6ፍጻሜ መጥቷል!
ፍጻሜ መጥቷል!
በአንቺ ላይ ተነሣሥቷል፤
እነሆ፤ ደርሷል!
7እናንት በምድሪቱ የምትኖሩ ሆይ፤
የጥፋት ፍርድ መጥቶባችኋል፤
ጊዜው ደርሷል፤
በተራሮች ላይ እልልታ ሳይሆን ሽብር የሚሰማበት ቀን ቀርቧል።
8እነሆ፤ መዓቴን በቅርብ ቀን አፈስስብሻለሁ፤
በአንቺ ላይ ቍጣዬን እፈጽምብሻለሁ፤
እንደ አካሄድሽ እፈርድብሻለሁ፤
ስለ ጸያፍ ተግባርሽም ሁሉ ተገቢውን ቅጣት እከፍልሻለሁ።
9በርኅራኄ ዐይን አልመለከትሽም፤
ምሕረት አላደርግልሽም፤
ስለ አካሄድሽና በመካከልሽ ስላለው ጸያፍ ተግባር፣
ተገቢውን ቅጣት እከፍልሻለሁ፤
በዚያ ጊዜ፣ የምቀሥፍ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ።

10“ ‘እነሆ ቀኑ ይኸው ደረሰ!
የጥፋት ፍርድ ተገልጧል፤
በትሩ አቈጥቍጧል፤
ትዕቢት አብቧል።
11ዐመፅ ዐድጋ
ወይም ዐመፀኛው የክፋት በትር

የክፋት በትር ሆነች፤
ከሕዝቡ አንድም አይተርፍም፤
ከሰዎቹ፣
ከሀብታቸውና እርባና ካለው ነገር
አንዳች አይቀርም።
12ጊዜው ደርሷል፤
ቀኑም ይኸው!
መዓት በሕዝቡ ሁሉ ላይ ስለ መጣ፣
የሚገዛ አይደሰት፤
የሚሸጥም አይዘን።
13ሁለቱ በሕይወት እስካሉ ድረስ
ሻጩ የሸጠውን መሬት አያስመልስም፤
ስለ መላው ሕዝብ የተነገረው ራእይ አይለወጥምና።
ከኀጢአታቸው የተነሣ ሕይወቱን ማትረፍ የሚችል አንድም አይገኝም።

14“ ‘መለከት ቢነፉም፣
ሁሉንም ነገር ቢያዘጋጁም፣
ወደ ጦርነት የሚሄድ አንድ እንኳ አይኖርም፤
መዓቴ በሕዝብ ሁሉ ላይ መጥቷልና።
15በውጭ ሰይፍ፣
በውስጥ ደግሞ ቸነፈርና ራብ አለ፤
በገጠር ያሉት
በሰይፍ ይወድቃሉ፤
በከተማ ያሉትም
በራብና በቸነፈር ያልቃሉ።
16ተርፈው ያመለጡት ሁሉ
በሸለቆ እንደሚኖሩ ርግቦች
ስለ ኀጢአታቸው እያለቀሱ
በተራራ ላይ ይሆናሉ።
17እጅ ሁሉ ይዝላል፤
ጕልበት ሁሉ ውሃ ይሆናል።
18ማቅ ይለብሳሉ፤
ሽብርም ይውጣቸዋል።
ፊታቸው ኀፍረት ይለብሳል፤
ራሳቸውም ይላጫል።

19“ ‘ብራቸውን በየጐዳናው ይጥላሉ፤
ወርቃቸውም እንደ ርኩስ ነገር ይቈጠራል።
በእግዚአብሔር የቍጣ ቀን
ብራቸውና ወርቃቸው
ሊያድናቸው አይችልም፤
በኀጢአት እንዲወድቁ ዕንቅፋት ሆኖባቸዋልና
በልተው አይጠግቡበትም፤ ሆዳቸውንም አይሞሉበትም።
20በውብ ዕንቋቸው ታብየዋል፤
ይህንም አስጸያፊ የጣዖት ምስሎቻቸውንና
ርኩስ ቅርጻ ቅርጾችን ለመሥራት ተጠቅመውበታል።
ስለዚህ እነዚህን ነገሮች ወደ ርኩሰት እለውጥባቸዋለሁ።
21ለባዕዳን ዝርፊያ፣ ለምድር ክፉዎችም ብዝበዛ አድርጌ አሳልፌ እሰጣለሁ፤
እነርሱም ያረክሱታል።
22ፊቴን ከእነርሱ እመልሳለሁ፤
እነርሱም የከበረውን ቦታዬን ያረክሳሉ፤
ወንበዴዎች ይገቡበታል፤
ያረክሱታልም።

23“ ‘ምድር በደም መፋሰስ፣
ከተማዪቱም በዐመፅ ተሞልታለችና
ሰንሰለት አዘጋጅ።
24እጅግ የከፉትን ከአሕዛብ አምጥቼ
ቤቶቻቸውን እንዲነጥቁ አደርጋለሁ፣
የኀያላኑንም ትዕቢት አጠፋለሁ፤
መቅደሳቸውም ይረክሳል።
25ሽብር በመጣ ጊዜ ሰላምን ይሻሉ፤
ነገር ግን አያገኟትም።
26ጥፋት በጥፋት ላይ፣
ወሬም በወሬ ላይ ይመጣል።
ራእይን ከነቢይ ለማግኘት ይጥራሉ፤
የሕግ ትምህርት ከካህኑ፣
ምክርም ከሽማግሌው ዘንድ ይጠፋል።
27ንጉሡ ያለቅሳል፤
መስፍኑ ተስፋ መቍረጥን ይከናነባል፤
የምድሪቱም ሕዝብ እጅ ትንቀጠቀጣለች።
የእጃቸውን እከፍላቸዋለሁ፤
ራሳቸው ባወጡት መስፈርት መሠረት
እፈርድባቸዋለሁ።
በዚያ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።’ ”

Copyright information for AmhNASV