Ezra 7:12-26

12
ዕዝ 7፥12-26 ላይ የሚገኘው ክፍል የተጻፈው በአረማይክ ቋንቋ ነው።
ከንጉሠ ነገሥት አርጤክስስ፤ ለሰማይ አምላክ ሕግ መምህር ለሆነው ለካህኑ ለዕዝራ፤

ሰላም ለአንተ ይሁን፤

13ካህናቱንና ሌዋውያኑን ጨምሮ በመንግሥቴ ውስጥ የሚኖርና ከአንተ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ የሚፈልግ ማንኛውም እስራኤላዊ መሄድ እንዲችል ይህን ትእዛዝ ሰጥቻለሁ። 14በእጅህ በሚገኘው በአምላክህ ሕግ መሠረት፣ ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም እንድትመረምር በንጉሡና በሰባት አማካሪዎቹ ተልከሃል። 15ከዚህም በላይ፣ ንጉሡና አማካሪዎቹ መኖሪያው በኢየሩሳሌም ለሆነው ለእስራኤል አምላክ በፈቃዳቸው የሰጡትን ብርና ወርቅ ይዘህ ሂድ፤ 16እንዲሁም ከመላው ባቢሎን አውራጃ የምታገኘውን ብርና ወርቅ በሙሉ፣ ሕዝቡና ካህናቱም በኢየሩሳሌም ላለው ለአምላካቸው ቤተ መቅደስ በፈቃዳቸው የሚሰጡትን መባ ሁሉ ይዘህ ሂድ። 17በዚህም ገንዘብ ወይፈኖችን፣ አውራ በጎችንና ጠቦቶችን፣ ከእህል ቍርባኖቻቸውና ከመጠጥ ቍርባኖቻቸው ጋር መግዛት እንዳለብህ አትርሳ፤ እነዚህንም በኢየሩሳሌም በሚገኘው በአምላካችሁ ቤተ መቅደስ መሠዊያ ላይ አቅርብ። 18ከዚህ የሚቀረውንም ብርና ወርቅ አንተና ወንድሞችህ አይሁድ እንደ አምላካችሁ ፈቃድ ደስ ለሚላችሁ ነገር ሁሉ አውሉት። 19ለአምላክህ ቤተ መቅደስ በዐደራ የተሰጠህንም ዕቃ ሁሉ በኢየሩሳሌም አምላክ ፊት አቅርብ። 20ከዚህም በላይ ለአምላክህ ቤተ መቅደስ ለመስጠት የምትፈልገውን ነገር ሁሉ ከንጉሡ ግምጃ ቤት መውሰድ ትችላለህ።

21በኤፍራጥስ ማዶ የምትገኙ በጅሮንዶች ሁሉ፣ የሰማይ አምላክ ሕግ መምህር የሆነው ካህኑ ዕዝራ የሚጠይቃችሁን ሁሉ በትጋት እንድትሰጡት እኔ ንጉሥ አርጤክስስ እነሆ አዝዣለሁ፤ 22እስከ አንድ መቶ መክሊት
3.4 ሜትሪክ ቶን ያህል ነው።
ብር፣ እስከ አንድ መቶ ቆሮስ
22 ኪሎ ሊትር ያህል ነው።
ስንዴ፣ እስከ አንድ መቶ ባዶስ
2.2 ኪሎ ሊትር ያህል ነው።
መስፈሪያ ወይን ጠጅ፣ እስከ አንድ መቶ ባዶስ የወይራ ዘይትና የሚፈለገውን ያህል ጨው ስጡት።
23የሰማይ አምላክ የሚያዘው ሁሉ፣ ለሰማይ አምላክ ቤተ መቅደስ በፍጹም ትጋት ይደረግ፤ በንጉሡና በልጆቹ መንግሥት ላይ ለምን ቍጣ ይውረድ? 24ደግሞም በካህናቱ፣ በሌዋውያኑ፣ በመዘምራኑ፣ በበር ጠባቂዎቹ፣ በቤተ መቅደሱ አገልጋዮች ወይም በሌሎቹ በዚህ በእግዚአብሔር ቤት ሠራተኞች ላይ ቀረጥ፣ ግብርና እጅ መንሻ ለመጣል ሥልጣን እንደሌላችሁ ይህን ዕወቁ።

25አንተም ዕዝራ ከአምላክህ እንደ ተሰጠህ ጥበብ መጠን፣ ከኤፍራጥስ ማዶ ለሚገኙት ሕዝቦች ሁሉ የአምላክህን ሕግ የሚያውቁ ዳኞችንና ፈራጆችን ሹምላቸው፤ ሕጉን የማያውቅ ሰው ቢኖር፣ አንተ ራስህ አስተምረው። 26ለአምላክህ ሕግና ለንጉሡ ሕግ የማይታዘዝ ማንኛውም ሰው፣ የሞት ወይም የስደት ወይም የንብረት መወረስ ወይም የእስራት ቅጣት ይፈጸምበት።

Copyright information for AmhNASV