‏ Hosea 1

1በይሁዳ ነገሥታት በዖዝያን፣ በኢዮአታም፣ በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመን እንዲሁም በእስራኤል ንጉሥ በዮአስ
በዕብራይስጥ ዮአስ የሚለው ቃል የኢዮአስ አማራጭ ትርጕም ነው
ልጅ በኢዮርብዓም ዘመን ወደ ብኤሪ ልጅ ወደ ሆሴዕ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው፤

የሆሴዕ ሚስትና ልጆቹ

2 እግዚአብሔር በሆሴዕ መናገር በጀመረ ጊዜ፣ እግዚአብሔር “ምድሪቱ ከእግዚአብሔር ተለይታ ታላቅ ምንዝርና እያደረገች ስለሆነ፣ ሄደህ አመንዝራ ሴት አግባ፤ የምንዝርና ልጆችንም ለራስህ ውሰድ” አለው። 3ስለዚህ እርሱ የዴቤላይምን ሴት ልጅ ጎሜርን አገባ፤ እርሷም ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደችለት።

4 እግዚአብሔርም ሆሴዕን እንዲህ አለው፤ “በኢይዝራኤል ስለ ተፈጸመው ግድያ የኢዩን ቤት በቅርቡ ስለምቀጣና የእስራኤልንም መንግሥት እንዲያከትም ስለማደርግ፣ ስሙን ኢይዝራኤል ብለህ ጥራው። 5በዚያም ቀን በኢይዝራኤል ሸለቆ፣ የእስራኤልን ቀስት እሰብራለሁ።”

6ጎሜር እንደ ገና ፀነሰች፤ ሴት ልጅም ወለደች፤ እግዚአብሔርም ሆሴዕን እንዲህ አለው፤ “ይቅር እላቸው ዘንድ ለእስራኤል ቤት ከእንግዲህ ስለማልራራላቸው፣ ስሟን ሎሩሃማ
ሎሩሃማ ማለት ያልተወደደች ማለት ነው
ብለህ ጥራት።
7ነገር ግን ለይሁዳ ቤት እራራለሁ፤ በቀስት ወይም በሰይፍ ወይም በጦርነት ወይም በፈረሶችና በፈረሰኞች ሳይሆን በአምላካቸው በእግዚአብሔር አድናቸዋለሁ።”

8ጎሜር፣ ሎሩሃማን ጡት ካስጣለች በኋላ ሌላ ወንድ ልጅ ወለደች። 9እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “ሎዓሚ
ሎዓሚ ማለት ሕዝቤ አይደለም ማለት ነው
ብለህ ጥራው፤ ምክንያቱም እናንተ ሕዝቤ አይደላችሁም፤ እኔም አምላካችሁ አይደለሁምና።

10“ይሁን እንጂ እስራኤላውያን ሊሰፈርና ሊቈጠር እንደማይችል እንደ ባሕር አሸዋ ይሆናሉ፤ ‘ሕዝቤ አይደላችሁም’ በተባሉበት ቦታ፣ ‘የሕያው አምላክ ልጆች’ ተብለው ይጠራሉ። 11የይሁዳ ሕዝብና የእስራኤል ሕዝብ እንደ ገና አንድ ይሆናሉ፤ አንድ መሪም ይሾማሉ፤ አንድ ሆነውም በምድሪቱ ይገንናሉ፤ የኢይዝራኤል ቀን ታላቅ ይሆናልና።

Copyright information for AmhNASV