Hosea 7

1እስራኤልን በምፈውስበት ጊዜ፣
የኤፍሬም ኀጢአት፣
የሰማርያም ክፋት ይገለጣል።
እነርሱ ያጭበረብራሉ፤
ሌቦች ቤቶችን ሰብረው ይገባሉ፤
ወንበዴዎችም በየመንገድ ይዘርፋሉ።
2ነገር ግን ክፉ ድርጊታቸውን ሁሉ እንደማስታውስ፣
እነርሱ አይገነዘቡም፤
ኀጢአታቸው ከብቧቸዋል፤
ሁልጊዜም በፊቴ ናቸው።

3“ንጉሡን በክፋታቸው፣
አለቆችንም በሐሰታቸው ያስደስታሉ።
4ሊጡ ቦክቶ ኩፍ እንደሚል፣
ዳቦ ጋጋሪው እሳት መቈስቈስ እስከማያስፈልገው ድረስ፣
እንደሚነድድ ምድጃ፣
ሁሉም አመንዝራ ናቸው።
5በንጉሣችን የበዓል ቀን፣
አለቆች በወይን ጠጅ ስካር ጋሉ፤
እርሱም ከፌዘኞች ጋር ተባበረ።
6ልባቸው እንደ ምድጃ የጋለ ነው፤
በተንኰል ይቀርቡታል፤
ቍጣቸው ሌሊቱን ሙሉ ይጤሳል፤
እንደሚነድድም እሳት በማለዳ ይንበለበላል።
7ሁሉም እንደ ምድጃ የጋሉ ናቸው፤
ገዦቻቸውን ፈጁ፤
ንጉሦቻቸው ሁሉ ወደቁ፤
ከእነርሱም ወደ እኔ የቀረበ ማንም የለም።

8“ኤፍሬም ከአሕዛብ ጋር ተደባለቀ፤
ኤፍሬም ያልተገላበጠ ቂጣ ነው።
9እንግዶች ጕልበቱን በዘበዙ፤
እርሱ ግን አላስተዋለም።
ጠጕሩም ሽበት አወጣ፤
እርሱ ግን ልብ አላለም።
10የእስራኤል ትዕቢት በራሱ ላይ መሰከረበት፤
ይህ ሁሉ ሆኖ ግን፣
ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር አልተመለሰም፤
እርሱንም አልፈለገም።

11“ኤፍሬም በቀላሉ እንደምትታለል፣
አእምሮም እንደሌላት ርግብ ነው፤
አንድ ጊዜ ወደ ግብፅ ይጣራል፤
ሌላ ጊዜ ደግሞ ወደ አሦር ይዞራል።
12ሲበርሩ፣ መረቤን በላያቸው እዘረጋለሁ፤
እንደ ሰማይ ወፎችም ጐትቼ አወርዳቸዋለሁ፤
ስለ ክፉ ሥራቸውም፣
በጕባኤ መካከል እቀጣቸዋለሁ።
13ወዮ ለእነርሱ፤
ከእኔ ርቀው ሄደዋልና!
ጥፋት ይምጣባቸው!
በእኔ ላይ ዐምፀዋልና።
ልታደጋቸው ፈለግሁ፤
እነርሱ ግን በእኔ ላይ ሐሰት ይናገራሉ።
14ከልባቸው ወደ እኔ አይጮኹም፤
ነገር ግን በዐልጋቸው ላይ ሆነው ያለቅሳሉ።
ስለ እህልና ስለ አዲስ የወይን ጠጅ
ይሰበሰባሉ፤
ነገር ግን ከእኔ ዘወር ብለዋል።
15እኔ አሠለጠንኋቸው፤ አጠነከርኋቸውም፤
እነርሱ ግን ዐደሙብኝ።
16ወደ ከንቱ ነገር ተመለሱ፤
ዒላማውን እንደ ሳተ ቀስት ናቸው፤
መሪዎቻቸው ስለ ክፉ ቃላቸው፣
በሰይፍ ይወድቃሉ፤
በዚህም ምክንያት በግብፅ ምድር፣
መዘባበቻ ይሆናሉ።”
Copyright information for AmhNASV