Isaiah 21
በባቢሎን ላይ የተነገረ ትንቢት
1በባሕሩ ዳር ባለው ምድረ በዳ ላይ የተነገረ ንግር፤ዐውሎ ነፋስ ከደቡብ እየጠራረገ እንደሚመጣ፣
ወራሪ ከአሸባሪ ምድር፣
ከምድረ በዳ ይመጣል።
2የሚያስጨንቅ ራእይ አየሁ፤
ከሓዲ አሳልፎ ይሰጣል፤ ዘራፊ ይዘርፋል።
ኤላም ሆይ፤ ተነሺ፤ ሜዶን ሆይ፤ ክበቢ፤
እርሷ ያደረሰችውን ሥቃይ ሁሉ አስቀራለሁ።
3ወገቤ በዚህ ሥቃይ ተሞላ፤
በምጥ ላይ እንዳለች ሴት ጭንቅ ያዘኝ፤
በሰማሁት ነገር ተንገዳገድሁ፤
ባየሁትም ነገር ተሸበርሁ።
4ልቤ ተናወጠ፤
ፍርሀት አንቀጠቀጠኝ፤
የጓጓሁለት ውጋጋን፣
ታላቅ ፍርሀት አሳደረብኝ።
5ማእዱን አሰናዱ፤
ምንጣፉን አነጠፉ፤
በሉ፤ ጠጡ!
እናንት ሹማምት ተነሡ፤
ጋሻውን በዘይት ወልውሉ!
6ጌታ እንዲህ አለኝ፤
“ሂድ፤ ጠባቂ አቁም፤
ያየውንም ይናገር፤
7በፈረሶች የሚሳብ፣
ሠረገሎችን ሲያይ፣
በአህያ ላይ የሚቀመጡትን፣
በግመል የሚጋልቡትን ሲመለከት፣
ያስተውል፤
በጥንቃቄም ያስተውል።”
8ጠባቂው ጮኸ፤ ▼
▼የሙት ባሕር ጥቅልልና የሱርስቱ ቅጅ ከዚህ ጋር ይስማማል፤ የማሶሬቱ ቅጅ ግን፣ አንበሳ ጮኸ ይላል።
እንዲህም አለ፤“ጌታ ሆይ፤ በየቀኑ ማማ ላይ ቆሜአለሁ፤
በየሌሊቱም በቦታዬ አለሁ።
9እነሆ፤ አንድ ሰው በፈረሶች በሚሳብ
በሠረገላ መጥቷል፤
እንዲህም ሲል መለሰ፣
‘ባቢሎን ወደቀች፣ ወደቀች!
የአማልክቷም ምስሎች ሁሉ፣
ተሰባብረው ምድር ላይ ወደቁ!’ ”
10በዐውድማ ላይ የተወቃህ ሕዝቤ ሆይ፤
ከሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣
ከእስራኤል አምላክ፣
የሰማሁትን እነግርሃለሁ።
በኤዶም ላይ የተነገረ ትንቢት
11ስለ ኤዶም የተነገረ ንግር፤አንዱ ከሴይር ጠርቶኝ፣
“ጠባቂ ሆይ፤ ሊነጋ ምን ያህል ቀረው?
ጠባቂ ሆይ፤ ሊነጋ ምን ያህል ቀረው?” አለኝ።
12ጠባቂውም መለሰ፤
“ይነጋል፤ ግን ተመልሶ ይመሻል፤
መጠየቅ ከፈለጋችሁ፣ ጠይቁ፤
ነገር ግን ተመልሳችሁ ኑ” አለ።
በዐረብ ላይ የተነገረ ትንቢት
13ስለ ዐረብ አገር የተነገረ ንግር፤እናንተ በዐረብ ዱር የምትሰፍሩ፣
የድዳን ሲራራ ነጋዴዎች፣
14ለተጠሙ ውሃ አምጡ።
በቴማን የምትኖሩ፣
ለስደተኞች ምግብ አምጡ።
15ከሰይፍ፣
ከተመዘዘ ሰይፍ፣
ከተደገነ ቀስት፣
ከተፋፋመ ጦርነት ሸሽተዋልና።
16ጌታም እንዲህ አለኝ፤ “በውል የተቀጠረ ሠራተኛ ቀን እንደሚቈጥር፣ የቄዳር ክብር በአንድ ዓመት ውስጥ ያበቃለታል። 17የተረፈው ቀስተኛ፣ የቄዳር ጦረኛ ጥቂት ይሆናል፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ተናግሯልና።”
Copyright information for
AmhNASV