‏ Jeremiah 28

ሐሰተኛው ነቢይ ሐናንያ

1በዚያው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ እንደ ነገሠ በአራተኛው ዓመት፣ አምስተኛ ወር፣ የገባዖኑ ሰው የዓዙር ልጅ ነቢዩ ሐናንያ በእግዚአብሔር ቤት፣ በካህናቱና በሕዝቡ ሁሉ ፊት እንዲህ አለኝ፤ 2“የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የባቢሎን ንጉሥ የጫነባችሁን ቀንበር እሰብራለሁ፤ 3የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከእግዚአብሔር ቤት ወደ ባቢሎን የወሰዳቸውን ዕቃዎች ሁሉ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ መልሼ አመጣለሁ። 4የይሁዳንም ንጉሥ የኢዮአቄምን ልጅ ኢኮንያንን፣
ወይም ኢዮአኪን ይላል።
ሌሎች ከይሁዳ ወደ ባቢሎን ተማርከው የተወሰዱትንም ሁሉ ወደዚህ ስፍራ እመልሳለሁ’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘የባቢሎን ንጉሥ የጫነባቸውን ቀንበር እሰብራለሁና።’ ”

5ነቢዩ ኤርምያስም በካህናቱና በእግዚአብሔር ቤት ቆመው በነበሩት ሕዝብ ሁሉ ፊት፣ ለነቢዩ ለሐናንያ እንዲህ ብሎ መለሰለት፤ 6“አሜን፤ እግዚአብሔር ያድርገው፤ የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃ ሁሉ፣ ተማርከው የተወሰዱትንም ምርኮኞች ሁሉ ከባቢሎን በመመለስ፣ እግዚአብሔር የተናገርኸውን ቃል ይፈጽም። 7ነገር ግን ለአንተም ለዚህም ሕዝብ የምናገረውን ቃል ስማ፤ 8ከአንተና ከእኔ በፊት ጥንት የተነሡ ነቢያት፣ በብዙ አገሮችና በታላላቅ መንግሥታት ላይ ስለ ጦርነት፣ ስለ ጥፋትና ስለ መቅሠፍት ትንቢት ተናግረዋል። 9ነገር ግን ስለ ሰላም ትንቢት የተናገረ ነቢይ እግዚአብሔር በእውነት እንደ ላከው የሚታወቀው የተናገረው ትንቢት ሲፈጸም ነው።”

10ነቢዩም ሐናንያ ቀንበሩን ከነቢዩ ኤርምያስ ዐንገት ወስዶ ሰበረው፤ 11በሕዝቡም ፊት፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ የባቢሎንን ንጉሥ የናቡከደነፆርን ቀንበር ከሕዝቡ ሁሉ ጫንቃ ላይ ልክ እንደዚህ እሰብራለሁ’ ” አለ። በዚህ ጊዜ፣ ነቢዩ ኤርምያስ ትቶት መንገዱን ቀጠለ።

12ነቢዩም ሐናንያ ቀንበሩን ከነቢዩ ከኤርምያስ ዐንገት ወስዶ ከሰበረ ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፤ 13“ሄደህ ለሐናንያ እንዲህ ብለህ ንገረው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ አንተ የዕንጨት ቀንበር ሰብረሃል፤ እኔ ግን በምትኩ የብረት ቀንበር እሠራለሁ። 14የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን እንዲያገለግሉ፣ በእነዚህ ሕዝቦች ላይ የብረት ቀንበር አደርጋለሁ፤ እነርሱም ይገዙለታል፤ በዱር አራዊት ላይ እንኳ ሥልጣን እሰጠዋለሁ።’ ”

15ነቢዩ ኤርምያስም ለነቢዩ ሐናንያ እንዲህ አለው፤ “ሐናንያ ሆይ፤ ስማ! እግዚአብሔር ሳይልክህ ይህ ሕዝብ በሐሰት እንዲታመን አድርገሃል፤ 16ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ከምድር ገጽ አስወግድሃለሁ፤ በእግዚአብሔርም ላይ ዐመፅ ተናግረሃልና፣ በዚህ ዓመት ትሞታለህ።’ ”

17ነቢዩም ሐናንያ በዚያው ዓመት በሰባተኛው ወር ሞተ።

Copyright information for AmhNASV