Jeremiah 34
ለሴዴቅያስ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ
1የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርና ሰራዊቱ ሁሉ፣ በግዛቱም ሥር ያሉ መንግሥታትና ሕዝቦች ሁሉ ኢየሩሳሌምንና በአካባቢዋ የሚገኙትን ከተሞች ይወጉ በነበረ ጊዜ፣ እንዲህ የሚል ቃል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ መጣ፤ 2“የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሴዴቅያስ ሄደህ እንዲህ ብለህ ንገረው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ይህችን ከተማ ለባቢሎን ንጉሥ አሳልፌ ልሰጣት ነው፤ እርሱም በእሳት ያቃጥላታል፤ 3አንተም በርግጥ ትያዛለህ፤ ዐልፈህም ለእርሱ ትሰጣለህ እንጂ ከእጁ አታመልጥም። የባቢሎንን ንጉሥ በዐይኖችህ ታየዋለህ፤ ፊት ለፊትም ያነጋግርሃል፤ ወደ ባቢሎንም ትሄዳለህ።4“ ‘ነገር ግን፣ የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ እግዚአብሔር ስለ አንተ እንዲህ ይላል፤ በሰይፍ አትሞትም፤ 5በሰላም ትሞታለህ። ሕዝቡ ከአንተ በፊት ለነበሩት ነገሥታት አባቶችህ ክብር በቀብራቸው ጊዜ እሳት እንዳነደዱ፣ በቀብርህም ጊዜ ስለ ክብርህ እሳት ያነድዳሉ፤ “ዋይ ዋይ ጌታችን!” እያሉም ያለቅሱልሃል፤ እኔ ራሴ ይህን ቃል ተናግሬአለሁና፤ ይላል እግዚአብሔር።’ ”
6ነቢዩ ኤርምያስ ይህን ሁሉ ለይሁዳ ንጉሥ ለሴዴቅያስ በኢየሩሳሌም ነገረው፤ 7በዚህም ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ ሰራዊት ኢየሩሳሌምንና የቀሩትን የይሁዳ ከተሞች ለኪሶንና ዓዜቃን እየወጋ ነበር፤ ከተመሸጉት የይሁዳ ከተሞችም የቀሩት እነዚሁ ብቻ ነበሩና።
የባሪያዎች ነጻ አለመውጣት
8ንጉሡ ሴዴቅያስ ባሪያዎችን ነጻ ለማውጣት ከኢየሩሳሌም ሕዝብ ሁሉ ጋር ቃል ኪዳን ካደረገ በኋላ፣ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ መጣ። 9እያንዳንዱ ሰው፣ ዕብራዊ የሆነውን ወንድ ባሪያውንና ዕብራዊት የሆነችውን ሴት ባሪያውን ነጻ ማውጣት ነበረበት፤ ማንም ሰው አይሁዳዊ ወንድሙን በባርነት መግዛት አልነበረበትም። 10በዚህ ቃል ኪዳን የተስማሙት ባለሥልጣኖችና ሕዝቡ ሁሉ ወንድ ወይም ሴት ባሪያዎቻቸውን ነጻ ለመልቀቅና ከእንግዲህ ባሪያ አድርገው ላይገዟቸው ተስማሙ። 11በኋላ ግን ሐሳባቸውን ቀይረው ነጻ የለቀቋቸው ባሪያዎቻቸውን እንዲመለሱ አደረጓቸው፤ እንደ ገናም ባሪያ አድርገው ገዟቸው።12ስለዚህ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፤ 13“የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በባርነት ከተገዙበት ከግብፅ ምድር ባወጣኋቸው ጊዜ፣ ከአባቶቻችሁ ጋር እንዲህ ብዬ ቃል ኪዳን አደረግሁ፤ 14“ራሱን በባርነት ለእናንተ የሸጠውን ዕብራዊ ወንድማችሁን እያንዳንዳችሁ በየሰባት ዓመቱ ነጻ ትለቅቃላችሁ፤ ስድስት ዓመት ከተገዛላችሁ በኋላ ነጻ ታወጡታላችሁ።” a አባቶቻችሁ ግን አልሰሙኝም ጆሯቸውንም ወደ እኔ አላዘነበሉም። 15እናንተም አሁን ንስሓ በመግባት በፊቴ ትክክለኛ ነገር አደረጋችሁ፤ እያንዳንዳችሁም ለወገኖቻችሁ ነጻነት ዐወጃችሁ፤ ስሜ በሚጠራበት ቤትም በፊቴ ቃል ኪዳን ገባችሁ። 16ነገር ግን ተመልሳችሁ ስሜን አረከሳችሁ፤ ወደ ፈለጉበት እንዲሄዱ ነጻ የለቀቃችኋቸውንም ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎቻችሁን መለሳችሁ፤ እንደ ገናም ባሪያዎቻችሁ አደረጋችኋቸው።’
17“ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ለወንድሞቻችሁና ለወገኖቻችሁ ነጻነት አላወጃችሁምና አልታዘዛችሁኝም። እንግዲህ እኔ ነጻነት ዐውጅላችኋለሁ፤’ ይላል እግዚአብሔር። ‘ይኸውም በሰይፍ፣ በቸነፈርና በራብ የምትወድቁበት ነጻነት ነው። ለምድር መንግሥታት ሁሉ መሠቀቂያ አደርጋችኋለሁ። 18ኪዳኔን ያፈረሱትንና በፊቴ የገቡትን የኪዳኑን ቃል ያልፈጸሙትን ሰዎች ሥጋውን ሁለት ቦታ ከፍለው በመካከሉ እንዳለፉት፣ እንደ እንቦሳው አደርጋቸዋለሁ። 19የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን መሪዎች፣ የቤተ መንግሥቱን ባለሟሎች፣ ካህናቱንና በእንቦሳው ሥጋ መካከል ያለፉትን ሕዝብ ሁሉ፣ 20ነፍሳቸውን ለሚሹ ጠላቶቻቸው አሳልፌ እሰጣለሁ፤ ሬሳቸውም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት መብል ይሆናል።
21“ ‘የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስንና መኳንንቱን፣ ነፍሳቸውን ለሚሹ ጠላቶቻቸው ይኸውም ለጊዜው እናንተን ከመውጋት ለተመለሱ ለባቢሎን ንጉሥ ሰራዊት አሳልፌ እሰጣለሁ። 22እነሆ፤ አዝዛቸዋለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር፤ ወደዚህችም ከተማ እንደ ገና እመልሳቸዋለሁ። እነርሱም ይወጓታል፤ ይይዟታል፤ በእሳትም ያቃጥሏታል። የይሁዳንም ከተሞች ሰው የማይኖርባቸው፣ ባድማ አደርጋቸዋለሁ።’ ”
Copyright information for
AmhNASV