Jeremiah 48
ስለ ሞዓብ የተነገረ መልክት
48፥29-36 ተጓ ምብ – ኢሳ 16፥6-12 1ስለ ሞዓብ፤የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“ናባው ትጠፋለችና ወዮላት፤
ቂርያታይም ትዋረዳለች፤ ትያዛለችም፤
ምሽጎች ▼
▼ወይም ሚሥጋብ
ይደፈራሉ፤ ይፈራርሳሉም።2ከእንግዲህ ሞዓብ አትከበርም፤
ሰዎች በሐሴቦን ▼
▼ሐሴቦን የሚለው የዕብራይስጡ ቃል አነባበብ መዶለት ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል ጋር ተመሳሳይ ነው።
ተቀምጠው፣‘ኑ ያቺን አገር እናጥፋት’ ብለው ይዶልቱባታል።
መድሜን ▼
▼መድሜን የሚለው የሞዓባውያን ከተማ ስም አነባበብ ጸጥ ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል ጋር ተመሳሳይ ነው።
ሆይ፤ አንቺም ደግሞ ጸጥ ትደረጊያለሽ፤ሰይፍም ያሳድድሻል።
3ከሖሮናይም የሚወጣውን ጩኸት፣
የመውደምና የታላቅ ጥፋት ድምፅ ስሙ!
4ሞዓብ ትሰበራለች፤
ልጆቿም ጩኸት ያሰማሉ። ▼
▼የዕብራይስጡና የሰብዓ ሊቃናት ትርጕሞች ለዞአር ያውጃሉ ይላሉ።
5ክፉኛ እያለቀሱ፣
ወደ ሉሒት ሽቅብ ይወጣሉ፤
ስለ ደረሰባቸውም ጥፋት መራራ ጩኸት እያሰሙ፣
ወደ ሖርናይም ቍልቍል ይወርዳሉ።
6ሽሹ፤ ሕይወታችሁንም አትርፉ!
በምድረ በዳ እንዳለ ቍጥቋጦ ▼
▼ወይም እንደ አሮኤር
ሁኑ።7በድርጊታችሁና በብልጽግናችሁ ስለምትታመኑ፣
እናንተም ትማረካላችሁ፤
ካሞሽም ከካህናቱና ከመኳንንቱ ጋር፣
በምርኮ ይወሰዳል።
8በእያንዳንዱ ከተማ ላይ አጥፊ ይመጣል፤
አንድም ከተማ አያመልጥም።
እግዚአብሔር ተናግሯልና፣
ሸለቆው ይጠፋል፤
ዐምባውም ይፈርሳል።
9በርራ እንድታመልጥ፣
ለሞዓብ ክንፍ ስጧት፤
ከተሞቿም ምንም እስከማይኖርባቸው ድረስ፣
ባድማ ▼
▼ወይም የተተወች ምድር እንድትሆን/በሞዓብ ላይ ጨው ነስንሱባት
ይሆናሉ።10“የእግዚአብሔርን ሥራ በቸልታ የሚያከናውን ርጉም ይሁን፤
ሰይፉን ደም ከማፍሰስ የሚከላከል የተረገመ ይሁን፤
11“ሞዓብ በአንቡላው ላይ እንዳረፈ የወይን ጠጅ፣
ከልጅነት ጀምሮ የተረጋጋ ነበረ፤
ከዕቃ ወደ ዕቃ አልተገላበጠም፤
በምርኮም አልተወሰደም፤
ቃናው እንዳለ ነው፤
መዐዛውም አልተለወጠም።
12ስለዚህ ዕቃውን የሚገለብጡ ሰዎችን
የምልክበት ጊዜ ይመጣል፤”
ይላል እግዚአብሔር።
“እነርሱም ይደፉታል፤
ዕቃውን ባዶ ያስቀራሉ፤
ማንቈርቈሪያዎቹንም ይሰባብራሉ።
13የእስራኤል ቤት፤
በቤቴል ታምኖ እንዳፈረ ሁሉ፣
ሞዓብም በካሞሽ ያፍራል።
14“እናንተ፣ ‘እኛ ተዋጊዎች ነን፤
በጦርነትም ብርቱ ነን’ ልትሉ እንዴት ቻላችሁ?
15ሞዓብ ትጠፋለች፤ ከተሞቿም ይወረራሉ፤
ምርጥ ወጣቶቿም ወደ መታረድ ይወርዳሉ፤”
ይላል ስሙ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሆነው ንጉሥ፤
16“የሞዓብ ውድቀት ተቃርቧል፤
ጥፋቱም ፈጥኖ ይመጣበታል።
17በዙሪያው የምትኖሩ ሁሉ፤
ዝናውን የምታውቁ ሁሉ አልቅሱለት፤
‘ብርቱው ከዘራ፣
የከበረው በትር እንዴት ሊሰበር ቻለ’ በሉ።
18“ሞዓብን የሚያጠፋ፣
በአንቺ ላይ ይመጣልና፤
የተመሸጉ ከተሞችሽንም ያጠፋልና፤
አንቺ የዲቦን ሴት ልጅ ሆይ፤
ከክብርሽ ውረጂ፤
በደረቅም መሬት ተቀመጪ።
19አንቺ በአሮዔር የምትኖሪ ሆይ፤
በመንገድ አጠገብ ቆመሽ ተመልከቺ፤
የሚሸሸውን ወንድ፣ የምታመልጠውንም ሴት፣
‘ምን ተፈጠረ?’ ብለሽ ጠይቂ።
20ሞዓብ በመፍረሱ ተዋርዷል፤
ዋይ በሉ፤ ጩኹ፤
የሞዓብን መደምሰስ፣
በአርኖን አጠገብ አስታውቁ።
21ፍርድ በዐምባው ምድር፦
በሖሎን፣ በያሳና በሜፍዓት ላይ፣
22በዲቦን፣ በናባውና በቤት ዲብላታይም ላይ፣
23በቂርያታይም፣ በቤት ጋሙልና በቤትምዖን ላይ፣
24በቂርዮትና በባሶራ ላይ፤
በሩቅና በቅርብ ባሉት በሞዓብ ከተሞች ሁሉ ላይ መጥቷል።
25የሞዓብ ቀንድ ▼
▼ቀንድ እዚህ ቦታ ኀይልን በትእምርትነት ይመለከታል።
ተቈርጧል፤እጁም ተሰባብሯል፤”
ይላል እግዚአብሔር።
26“እግዚአብሔርን ንቋልና፣
ሞዓብን በመጠጥ አስክሩት።
ሞዓብ በትፋቱ ላይ ይንከባለል፤
ለመዘባበቻም ይሁን።
27በእስራኤል ላይ ስታላግጥ አልነበረምን?
ስለ እርሷ በተናገርህ ቍጥር፣
እያቃለልሃት ራስህን የምትነቀንቀውስ፣
ከሌቦች ጋር ስትሰርቅ ተይዛለችን?
28እናንተ በሞዓብ የምትኖሩ ሆይ፤
ከከተማ ወጥታችሁ በዐለት መካከል ኑሩ፤
በገደል አፋፍ ላይ ጐጆዋን እንደምትሠራ፣
እንደ ርግብ ሁኑ።
29“ስለ ሞዓብ ትዕቢት፣
ስለ እብሪቱና ስለ ኵራቱ፣
ስለ ትምክሕቱና ስለ መጓደዱ፣
ስለ ልቡም ማበጥ ሰምተናል።
30መዳፉን ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን ከንቱ ነው፤”
ይላል እግዚአብሔር።
“ጕራውም ፋይዳ አይኖረውም።
31ስለዚህ ለሞዓብ አለቅሳለሁ፤
ለሞዓብ ምድር ሁሉ ዋይ እላለሁ፤
ለቂርሔሬስ ሰዎችም የልቅሶ ድምፅ አሰማለሁ።
32የሴባማ ወይን ሆይ፤
ለኢያዜር ካለቀስሁት እንኳ ይልቅ አለቅስልሻለሁ፤
ቅርንጫፎችሽ እስከ ባሕሩ ተዘርግተዋል፤
እስከ ኢያዜርም ደርሰዋል፤
ለመከር በደረሰው ፍሬሽና በወይንሽ ላይ፣
አጥፊው መጥቷል።
33ከሞዓብ የአትክልት ቦታና ዕርሻ፣
ሐሤትና ደስታ ርቋል፤
የወይን ጠጅ ከመጭመቂያው እንዳይወርድ አድርቄዋለሁ፤
በእልልታ የሚጨምቀውም አይገኝም፤
በዚያ ድምፅ ቢሰማም፣
የእልልታ ድምፅ አይደለም።
34“ከሐሴቦን እስከ ኤልያሊና እስከ ያሀጽ፣
ከዞዓር እስከ ሖሮናይም፣ እስከ ዔግላት ሺሊሺያ ድረስ፣
ጩኸታቸው ከፍ ብሎ ይሰማል፤
የኔሞሬም ውሃ እንኳ ደርቋልና።
35በመስገጃ ኰረብቶች ላይ የሚሠዉትን፣
ለአማልክታቸው የሚያጥኑትን፣
ከሞዓብ አጠፋለሁ፤”
ይላል እግዚአብሔር፤
36“ስለዚህ ልቤ ለሞዓብ እንደ ዋሽንት ያንጐራጕራል፤
ለቂርሔሬስ ሰዎችም እንደ ዋሽንት ያንጐራጕራል።
ያከማቹት ንብረት ጠፍቷልና።
37የእያንዳንዱ ሰው ራስ፣
ጢምም ሁሉ ተላጭቷል፤
እጅ ሁሉ ተቸፍችፏል፤
ወገብም ሁሉ ማቅ ታጥቋል።
38በሞዓብ ቤቶች ጣራ ሁሉ ላይ፣
በሕዝብም አደባባዮች፣
ሐዘን እንጂ ሌላ የለም፤
እንደማይፈለግ እንስራ፣
ሞዓብን ሰብሬአለሁና፤”
ይላል እግዚአብሔር።
39“እንዴት ተንኰታኰተ! ምንኛስ አለቀሱ!
ሞዓብ እንዴት ዐፍሮ ጀርባውን አዞረ!
ሞዓብ የመሰደቢያ፣
በዙሪያው ላሉትም ሁሉ የሽብር ምልክት ሆነ።”
40 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“እነሆ፤ እንደ ንስር ተወርውሮ ይወርድበታል፤
ክንፎቹንም በሞዓብ ላይ ይዘረጋል።
41ከተሞቹ ▼
▼ወይም ቂርያት
ይወረራሉ፤ምሽጎቹም ይያዛሉ፤
በዚያን ቀን የሞዓብ ጦረኞች ልብ፣
በምጥ እንደ ተያዘች ሴት ልብ ይሆናል።
42ሞዓብ እግዚአብሔርን አቃልሏልና ይጠፋል፤
መንግሥትነቱም ይቀራል።
43የሞዓብ ሕዝብ ሆይ፤
ሽብርና ጕድጓድ፣ ወጥመድም ይጠብቅሃል፤”
ይላል እግዚአብሔር።
44“ከሽብር የሚሸሽ ሁሉ፣
ጕድጓድ ውስጥ ይገባል፤
ከጕድጓዱም የሚወጣ፣
በወጥመድ ይያዛል፤
በሞዓብ ላይ፣
የቅጣቱን ዓመት አመጣለሁና፣”
ይላል እግዚአብሔር።
45“የሞዓብን ግንባር፣
የደንፊዎችን ዐናት የሚያቃጥል፣
እሳት ከሐሴቦን፣
ነበልባል ከሴዎን ቤት ወጥቷልና፤
ኰብላዮች በሐሴቦን ጥላ ሥር፣
ተስፋ ቈርጠው ቆመዋል።
46ሞዓብ ሆይ፤ ወዮልህ!
የካሞሽ ሕዝብ ተደምስሷል፤
ወንዶች ልጆችህ በምርኮ ተወስደዋል፤
ሴቶች ልጆችህም ተግዘዋል።
47“ነገር ግን የኋላ ኋላ፣
የሞዓብን ምርኮ እመልሳለሁ፤”
ይላል እግዚአብሔር።
በሞዓብ ላይ የተወሰነው ፍርድ ይኸው ነው።
Copyright information for
AmhNASV