‏ Lamentations 5

1እግዚአብሔር ሆይ፤ በእኛ ላይ የደረሰውን ዐስብ፤
ውርደታችንን እይ፤ ተመልከትም።
2ርስታችን ለመጻተኞች፣
ቤቶቻችን ለባዕዳን ዐልፈው ተሰጡ።
3ወላጅ አልባና አባት የሌላቸው ሆንን፤
እናቶቻችን እንደ መበለቶች ሆኑ።
4ለምንጠጣው ውሃ መክፈል ነበረብን፤
ዕንጨታችንንም የምናገኘው በግዢ ነበር።
5የሚያሳድዱን ከተረከዞቻችን ሥር ናቸው፤
ተጨንቀናል ዕረፍትም ዐጥተናል።
6እንጀራ እንጠግብ ዘንድ፣
ለአሦርና ለግብፅ እጃችንን ሰጠን።
7አባቶቻችን ኀጢአት ሠርተው ዐለፉ፤
እኛም የእነርሱን ቅጣት ተሸከምን።
8ባሮች ሠልጥነውብናል፤
ከእጃቸው ነጻ የሚያወጣን ማንም የለም።
9በምድረ በዳ ካለው ሰይፍ የተነሣ፣
በሕይወታችን ተወራርደን እንጀራ አገኘን።
10ቈዳችን እንደ ምድጃ ጠቍሯል፤
በራብም ተቃጥሏል።
11ሴቶች በጽዮን፣
ደናግል በይሁዳ ከተሞች ተደፈሩ።
12መሳፍንት በእነርሱ እጅ ተሰቀሉ፤
ሽማግሌዎችም አልተከበሩም።

13ጕልማሶች ወፍጮ እንዲፈጩ ተገደዱ፤
ወንዶች ልጆች በዕንጨት ሸክም ተንገዳገዱ።
14ሽማግሌዎች ከከተማዪቱ በር ሄደዋል፤
ጕልማሶች ዝማሬያቸውን አቁመዋል።
15ደስታ ከልባችን ጠፍቷል፤
ጭፈራችን ወደ ልቅሶ ተለውጧል።
16አክሊላችን ከራሳችን ላይ ወድቋል፤
ወዮልን፤ ኀጢአት ሠርተናልና!
17ከዚህ የተነሣ ልባችን ደከመ፤
ከእነዚህ የተነሣም ዐይናችን ፈዘዘ፤
18ባዶዋን የቀረችው የጽዮን ተራራ፣
የቀበሮዎች መፈንጫ ሆናለችና።

19አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ለዘላለም ትገዛለህ፤
ዙፋንህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል።
20ስለ ምን ፈጽመህ ትረሳናለህ?
ስለምንስ ለረዥም ጊዜ ትተወናለህ?
21 እግዚአብሔር ሆይ፤ ወደ አንተ መልሰን፤ እኛም እንመለሳለን፤
ዘመናችንን እንደ ቀድሞው አድስ፤
22ፈጽመህ ካልጣልኸን፣
ከመጠን በላይ ካልተቈጣኸን።
Copyright information for AmhNASV