Numbers 17

የአሮን በትር ማቈጥቈጥ

1 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2“ለእስራኤላውያን ንገራቸውና ከየነገዱ አለቆች አንዳንድ፣ በአጠቃላይ ዐሥራ ሁለት በትር ተቀበል፤ የያንዳንዱንም ሰው ስም በየበትሩ ላይ ጻፈው። 3ለያንዳንዱ የነገድ አለቃ አንዳንድ በትር መኖር ስላለበት በሌዊ በትር ላይ የአሮንን ስም ጻፍ። 4በትሮቹንም እኔ ከአንተ ጋር በምገናኝበት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ከምስክሩ ፊት ለፊት አስቀምጣቸው። 5እኔ የምመርጠው ሰው በትርም ታቈጠቍጣለች፤ እስራኤላውያን በእናንተ ላይ ነጋ ጠባ የሚያደርጉትንም ማጕረምረም በዚህ እገታለሁ።”

6ሙሴም ለእስራኤላውያን ተናገራቸው፤ አለቆቻቸውም በቀደሙት በያንዳንዱ አባቶች ስም ዐሥራ ሁለት በትር ሰጡት፤ የአሮን በትርም በበትሮቹ መካከል ነበረች። 7ሙሴም በትሮቹን ወስዶ በምስክሩ ድንኳን ውስጥ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት አኖራቸው።

8በማግስቱም ሙሴ ወደ ምስክሩ ድንኳን ሲገባ በሌዊ ቤት ስም የቀረበችው የአሮን በትር ማቈጥቈጥ ብቻ ሳይሆን እንቡጥ አውጥታ፣ አብባና ለውዝ አፍርታ አገኛት። 9ከዚያም ሙሴ በትሮቹን ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት አውጥቶ ወደ እስራኤላውያን ሁሉ አመጣቸው፤ እነርሱም አዩ፤ እያንዳንዱም ሰው የየራሱን በትር ወሰደ።

10 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “የአሮን በትር ለዐመፀኞቹ ምልክት እንድትሆን መልሰህ በምስክሩ ፊት ለፊት አኑራት፤ እነርሱ እንዳይሞቱም በእኔ ላይ የሚያደርጉትን ማጕረምረም ይህ ይገታዋል” አለው። 11ሙሴም ልክ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳዘዘው አደረገ።

12ከዚያም እስራኤላውያን ሙሴን እንዲህ አሉት፤ “እነሆ መሞታችን ነው! ጠፋን፤ ሁላችንም መጥፋታችን ነው! 13ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ማደሪያ የሚጠጋ እንኳ ማንኛውም ሰው ቢሆን ይሞታል፤ ሁላችንም ልንጠፋ ነው እንዴ?”

Copyright information for AmhNASV