Numbers 19

የመንጻት ሥርዐት ውሃ

1 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ 2እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዘው፣ ሕጉ የሚጠይቀው ሥርዐት ይህ ነው፤ እንከን ወይም ነውር የሌለባትንና ቀንበር ተጭኖባት የማያውቅ አንዲት ቀይ ጊደር እንዲያመጡልህ ለእስራኤላውያን ንገራቸው። 3ለካህኑ ለአልዓዛርም ስጠው፤ ከሰፈሩ አውጥተውም በፊቱ ይረዷት። 4ከዚያም ካህኑ አልዓዛር ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ፣ ወደ መገናኛው ድንኳን ፊት አቅጣጫ ሰባት ጊዜ ይርጨው። 5እርሱ እየተመለከተም ጊደሯን ያቃጥሏት፤ ቈዳዋም፣ ሥጋዋም፣ ደሟም፣ ፈርሷም ጭምር ይቃጠል። 6ካህኑ የዝግባ ዕንጨት፣ ሂሶጵና ብሩህ ቀይ ክር ወስዶ ጊደሪቱ በምትቃጠልበት እሳት ውስጥ ይጨምር። 7ከዚህ በኋላ ካህኑ ልብሱን በውሃ ማጠብ፣ ሰውነቱንም መታጠብ አለበት፤ ከዚያም ወደ ሰፈሩ ሊመለስ ይችላል፤ ይሁን እንጂ በሥርዐቱ መሠረት እስከ ማታ ድረስ የረከሰ ይሆናል። 8የሚያቃጥለውም ሰው እንደዚሁ ልብሱን ማጠብ፣ ሰውነቱንም በውሃ መታጠብ አለበት፤ እርሱም ደግሞ እስከ ማታ ድረስ የረከሰ ይሆናል።

9“ንጹሕ የሆነ ሰው የጊደሯን ዐመድ ዐፍሦ ከሰፈሩ ውጭ በመውሰድ በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ በሆነ ስፍራ ያኑረው፤ ይህም ለመንጻቱ ውሃ እንዲውል በእስራኤል ማኅበረ ሰብ የሚጠበቅ ይሆናል፤ ከኀጢአትም ለመንጻት ይጠቅማል። 10የጊደሯን ዐመድ የሚያፈስሰውም ሰው እንደዚሁ ልብሱን ማጠብ አለበት፤ ያም ሰው እስከ ማታ ድረስ የረከሰ ይሆናል፤ ይህም ለእስራኤላውያን እንዲሁም በመካከላቸው ለሚኖሩ መጻተኞች የሚሆን ዘላለማዊ ሥርዐት ነው።

11“የሞተን ሰው በድን የሚነካ ማንኛውም ሰው እስከ ሰባት ቀን የረከሰ ይሆናል። 12በሦስተኛውና በሰባተኛውም ቀን ሁለመናውን በውሃው ያንጻ፤ ንጹሕም ይሆናል። በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ሁለመናውን ካላነጻ ግን ንጹሕ አይሆንም። 13የሞተን ሰው በድን ነክቶ ራሱን ያላነጻ ማንኛውም ሰው የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ማደሪያ ያረክሳል፤ ያም ሰው ከእስራኤል ተለይቶ ይጥፋ። የሚያነጻው ውሃ ስላልተረጨበት ርኩስ ነው፤ ከርኩሰቱም አልተላቀቀም።

14“አንድ ሰው በድንኳን ውስጥ በሚሞትበት ጊዜ የሚፈጸመው ሥርዐት የሚከተለው ነው፤ ወደ ድንኳኑ የሚገባም ሆነ በዚያ ውስጥ ያለ ማንኛውም ሰው እስከ ሰባት ቀን ድረስ የረከሰ ይሆናል፤ 15እንዲሁም ያልተከደነ ማንኛውም ክፍት ዕቃ የረከሰ ይሆናል።

16“ሜዳ ላይ በሰይፍ የተገደለውን ወይም እንዲሁ የሞተውን ወይም ደግሞ ዐፅም ወይም መቃብር የሚነካ ማንኛውም ሰው እስከ ሰባት ቀን ድረስ የረከሰ ይሆናል።

17“ለረከሰውም ሰው፣ ለማንጻት ከተቃጠለው የጊደር ዐመድ ላይ ማሰሮ ውስጥ በማድረግ በላዩ የምንጭ ውሃ ይጨምሩበት። 18ከዚያም በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ የሆነ ሰው ሂሶጵ ወስዶ በውሃው ውስጥ ከነከረው በኋላ ድንኳኑን፣ በውስጡ ያሉትን ዕቃዎች ሁሉ፣ እዚያ የነበሩትንም ሰዎች ሁሉ ይርጫቸው። እንዲሁም የሰው ዐፅም ወይም መቃብር ወይም ደግሞ የተገደለውን ወይም እንዲሁ የሞተውን ሰው የነካው ማንኛውንም ሰው ይርጭ። 19የነጻው ሰው ያልነጻውን ሰው በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ይርጨው፤ በሰባተኛው ቀን ያንጻው፤ የሚነጻውም ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ገላውንም በውሃ ይታጠብ፤ ማምሻውም ላይ የነጻ ይሆናል። 20ይሁን እንጂ አንድ የረከሰ ሰው ራሱን ሳያነጻ ከቀረ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) መቅደስ አርክሷልና ከማኅበረ ሰቡ ተለይቶ ይጥፋ፤ የሚያነጻው ውሃ ያልተረጨበት ስለሆነ ርኩስ ነው። 21ይህም ለእነርሱ የዘላለም ሥርዐት ነው።

“የሚያነጻውን ውሃ የሚረጨውም ሰው ልብሱን ይጠብ፤ የሚያነጻውንም ውሃ የሚነካ ማንኛውም ሰው እስከ ማምሻው ድረስ የረከሰ ይሆናል።
22የረከሰ ሰው የሚነካው ማናቸውም ነገር ይረክሳል፤ ይህን የነካ ሰው ደግሞ እስከ ማምሻው ድረስ የረከሰ ይሆናል።”

Copyright information for AmhNASV