Numbers 30

ስእለት

1ሙሴ ለእስራኤል የነገድ አለቆች እንዲህ አላቸው፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዘው ይህ ነው፤ 2አንድ ሰው ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ስእለት በሚሳልበት ወይም አንድ ነገር ለማድረግ በመሐላ ራሱን ግዴታ ውስጥ በሚያስገባበት ጊዜ ቃሉን ሳያጥፍ ያለውን ሁሉ መፈጸም አለበት።

3“በአባቷ ቤት የምትኖር ሴት ልጅ ለእግዚአብሔር (ለያህዌ) ስእለት ብትሳል ወይም አንድ ነገር ለማድረግ በመሐላ ራሷን ግዴታ ውስጥ ብታስገባ፣ 4አባቷም መሳሏን ወይም ራሷን ግዴታ ውስጥ ማስገባቷን ሰምቶ ምንም ነገር ሳይላት ቢቀር፣ ስእለቶቿ በሙሉ፣ ራሷንም ግዴታ ውስጥ ያስገባችባቸው ነገሮች ሁሉ መፈጸም ይኖርባቸዋል። 5አባቷ ይህንኑ ሰምቶ ከከለከላት ግን የትኛውም ስእለቷ ወይም ራሷን ግዴታ ውስጥ ያስገባችበት መሐላ አይያዝባትም፤ የከለከላት አባቷ ስለሆነ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነጻ ያደርጋታል።

6“እንዲሁም ከተሳለች ወይም አምልጧት ተናግራ ራሷን ግዴታ ውስጥ ካስገባች በኋላ ባል ብታገባ፣ 7ባሏም ሰምቶ ምንም ነገር ሳይላት ቢቀር ስእለቶቿ ወይም ራሷን ግዴታ ውስጥ ያስገባችባቸው ነገሮች መፈጸም ይኖርባቸዋል። 8ሆኖም ባሏ ይህንኑ ሰምቶ ከከለከላት ግን ለመፈጸም የተሳለችውንም ሆነ አምልጧት ተናግራ ራሷን ግዴታ ውስጥ ያስገባችበትን ነገር ስለሚያስቀር እግዚአብሔር (ያህዌ) ከዚህ ነጻ ያደርጋታል።

9“ባሏ የሞተባት ወይም ከባሏ የተፋታች ሴት የትኛውም ስእለቷ ወይም የገባችበት ግዴታ ሁሉ የጸና ይሆናል።

10“ከባሏ ጋር የምትኖር ሴት ብትሳል ወይም አንድ ነገር ለማድረግ በመሐላ ራሷን ግዴታ ውስጥ ብታስገባና 11ባሏም ይህንኑ ሰምቶ ምንም ነገር ባይላትና ባይከለክላት ግን ስእለቶቿም ሆኑ ለማድረግ ራሷን ግዴታ ውስጥ ያስገባችባቸው ነገሮች ሁሉ የጸኑ ይሆናሉ። 12ባሏ ሰምቶ እንዲቀሩ ካደረገ ግን ስእለቶቿንም ሆነ ለማድረግ ቃል የገባቻቸውን ነገሮች የመፈጸም ግዴታ የለባትም፤ ባሏ እንዲቀሩ ስላደረጋቸው እግዚአብሔር (ያህዌ) ነጻ ያደርጋታል። 13የትኛውንም ስእለቷን ወይም ራሷን ለመከላከል በመሐላ የታሰረችበትን ሁሉ ባሏ ሊያጸናው ወይም ሊያፈርሰው ይችላል። 14ይሁን እንጂ ባሏ ግን ስለ ጕዳዩ ከዕለት ወደ ዕለት ምንም ነገር ሳይላት ቢቀር ስእለቶቿን ወይም ራሷን ግዴታ ውስጥ ያስገባችባቸውን ነገሮች ሁሉ እያጸናላት ነው ማለት ነው፤ ስለ ነገሮቹ ሰምቶ ምንም ነገር ሳይላት በመቅረቱ አጽንቶላታል። 15ስለ ነገሮቹ ከሰማ በኋላ እንዲቀሩ ካደረገ ግን ለፈጸመችው በደል በኀላፊነት የሚጠየቀው ራሱ ነው።”

16እነዚህ እንግዲህ በባልና በሚስት፣ በአባትና አብራው በቤት ውስጥ በምትኖር ልጁ መካከል ያለውን ግንኙነት አስመልክቶ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለሙሴ የሰጠው ሥርዐቶች ናቸው።

Copyright information for AmhNASV