‏ Ruth 3

ቦዔዝና ሩት በእህል ዐውድማው ላይ

1ከዚህ በኋላ ዐማቷ ኑኃሚን ሩትን እንዲህ አለቻት፤ “ልጄ ሆይ፤ የሚመችሽን ቤት
ወይም የምታርፊበትን
እንድፈልግልሽ አይገባኝምን?
2ከሴቶች ሠራተኞቹ ጋር አብረሽ የነበርሽበት ቦዔዝ፣ ዘመዳችን አይደለምን? ዛሬ ማታ በዐውድማው ላይ ገብስ ያበራያል፤ 3ተጣጠቢ፤ ሽቶ ተቀቢ፤ እንዲሁም የክት ልብስሽን ልበሺ፤ ከዚያም ወደ ዐውድማው ውረጂ፤ ይሁን እንጂ በልቶና ጠጥቶ እስኪያበቃ ድረስ፣ እዚያ መሆንሽን እንዳያውቅ ይሁን። 4በተኛም ጊዜ፣ የሚተኛበትን ቦታ ልብ ብለሽ እዪና ሄደሽ እግሩን ገልጠሽ ተኚ፤ ከዚያም የምታደርጊውን ራሱ ይነግርሻል።”

5ሩትም፣ “ያልሽውን ሁሉ አደርጋለሁ” አለቻት። 6ስለዚህ ተነሥታ ወደ ዐውድማው ወረደች፤ ዐማቷ አድርጊ ያለቻትንም ሁሉ አደረገች።

7ቦዔዝ በልቶ ጠጥቶ ከጨረሰና ደስም ከተሰኘ በኋላ፣ ራቅ ካለው የእህል ክምር አጠገብ ለመተኛት ሄደ። ሩት በቀስታ ከአጠገቡ ደረሰች፤ እግሩንም ገልጣ ተኛች። 8እኩለ ሌሊት ላይ ሰውየውን አንዳች ነገር አስደነገጠው፤ ገልበጥ ሲልም አንዲት ሴት እግርጌው ተኝታ አገኘ።

9እርሱም፣ “አንቺ ማነሽ?” ሲል ጠየቀ። እርሷም፣ “እኔ አገልጋይህ ሩት ነኝ፤ መቤዠት የሚገባህ ቅርብ የሥጋ ዘመድ አንተ ነህና ልብስህን ጣል አድርግብኝ” አለችው።

10እርሱም መልሶ እንዲህ አላት፤ “ልጄ ሆይ፤ እግዚአብሔር ይባርክሽ፤ ከዚህ በፊት ካደረግሽው ይልቅ ያሁኑ በጎነትሽ ይበልጣል፤ ባለጠጋም ሆነ ድኻ፣ ወጣት ወንድ ፈልገሽ አልሄድሽምና። 11አሁንም ልጄ ሆይ፤ አትፍሪ፤ የምትጠይቂውን ሁሉ አደርግልሻለሁ፤ አንቺ ምግባረ መልካም ሴት መሆንሽንም የአገሬ ሰው ሁሉ ያውቀዋል። 12ምንም እንኳ እኔ ቅርብ የሥጋ ዘመድ መሆኔ የተረጋገጠ ቢሆንም፣ ከእኔ ይልቅ መቤዠት የሚገባው ቅርብ የሥጋ ዘመድ አለ። 13ከዚህ ዕደሪ፤ ሲነጋም ሰውየው ሊቤዥሽ ከፈለገ፣ መልካም ነው፤ ይቤዥሽ፤ የማይፈልግ ከሆነ ግን በሕያው እግዚአብሔር እምላለሁ፤ እኔ እቤዥሻለሁ፤ እስኪነጋም ድረስ እዚሁ ተኚ።”

14ስለዚህም ሩት እስኪነጋ ድረስ እግርጌው ተኛች፤ ዳሩ ግን ማንም ሰው ተለይቶ ሊታወቅ በማይችልበት ሰዓት ቀደም ብላ ተነሣች፤ እርሱም፣ “ሴት ወደዚህ ዐውድማ መምጣቷ እንዳይታወቅ” አላት።

15እንዲሁም፣ “በላይሽ የደረብሽውን ልብስ አቅርቢልኝ፤ ዘርግተሽም ያዢው” አላት፤ ዘርግታ እንደ ያዘችም ስድስት መስፈሪያ ገብስ ሰፍሮ አሸከማት፤ ከዚያም ወደ ከተማ ተመለሰች
አብዛኞቹ የዕብራይስጥ ቅጆች፣ ቩልጌትና ሱርስት ከዚህ ጋር ይስማማሉ፤ አንዳንድ የዕብራይስጥ ቅጆች ግን ይነገረኝና ይላሉ።


16ሩት ወደ ዐማቷ እንደ ተመለሰች፣ ኑኃሚን፣ “ልጄ ሆይ፤ የሄድሽበት ጕዳይ እንዴት ሆነ?” ብላ ጠየቀቻት።

ሩትም ቦዔዝ ያደረገላትን ሁሉ ነገረቻት፤
17ቀጥላም፣ “ ‘ወደ ዐማትሽ ባዶ እጅሽን አትመለሺ’ በማለት ይህን ስድስት መስፈሪያ ገብስ ሰጠኝ” አለቻት።

18ኑኃሚንም፣ “ልጄ ሆይ፤ የሚሆነውን ነገር እስክታውቂ ድረስ ታገሺ፤ ጕዳዩ ዛሬውኑ እልባት ካላገኘ ሰውየው አያርፍም” አለቻት።

Copyright information for AmhNASV